ምርት የማከማቻ ጎተራዎች ከተባይና መሰል በሽታዎች በጸዳ መልኩ በማዘጋጀት የሚፈለገዉን የምግብ ዋስትና በዘላቂነት ማረጋገጥ እንደሚገባ በጉራጌ ዞን የእዣ ወረዳ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የምርት ብክነት እንዳይኖርና በዘርፉ የሚፈለገዉን ዉጤት እንዲመጣ አርሶአደሩ ምርት አሰባሰቡ ላይ ከመቼዉም ጊዜ በላይ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበትም ተመላክቷል።

የእዣ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዘዉዱ ዱላ እንዳሉት በግብርና ዘርፍ የሚፈለገዉ ዉጤት ለማምጣት ከጊዜ ወደ ጊዜ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ሲሆን በዚህም የአርሶአደሩ ምርትና ምርታማነት እያደገ ይገኛል።

በወረዳው በመኸር ወቅት 5ሺህ 4 መቶ 90 ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች መሸፈን የተቻለ ሲሆን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

አሁን ላይ የቁም ሰብል ትመና እየተካሄደ እንደሆነና ጥሩ የሚባል ዉጤት እየታየ ይገኛል ያሉት ኃላፊዉ የአርሶአደሩን ምርትና ምርታማነት ከማሳደግ ጋር ቀደም ባሉት ጊዜያት የነበሩ ዉስንነቶች በመቅረፍ የሚፈለገዉ ዉጤት እንዲመጣ በትኩረት እየተሰራ እንደሆነም አመላክተዋል።

በሁሉም ሰብል ምርታማነት በሄክታር በሄክታር 32 ኩንታል ምርት በማድረስ 175 ሺህ 6 መቶ 80 ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

በወረዳዉ በቆላዉ አካባቢ የደረሰ የጤፍ ሰብል የማንሳት ስራ እየተከናወነ መሆኑም አብራርተዉ በደጋዉና በሌሎች አካባቢዎች ምርት የእርጥበት መጠኑ በሚፈለገዉ ደረጃ ባለመጠናቀቁ የተነሳ ሰብልን ሙሉበሙሉ መሰብሰብ እንዳልተቻለ አስረድተዋል።

የምርት ብክነት እንዳይኖር በየደረጃዉ የተዋቀሩ አደረጃጀቶች ማለትም ልማቱን ሊያፋጥኑ የሚችሉ የአንድ ለአምስትና የአንድ ለአስር አደረጃጀቶች እንዲሁም የልማት ቡድንና መሰል አደረጃጀቶች እንዲሁም የቤተሰብ ጉልበት በተገቢዉ ተጠቅመዉ ምርት ሳይባክን መሰብሰብ ይኖርባቸዋል ብለዋል።

በጣም ሰፋፊ ማሳዎች ሌሎች አጋዥ ቴክኖሎጂዎች በመጠቀም አርሶአደሩ ያለምንም መዘናጋት ምርት የሚሰበስብበት ሁኔታ አጠናክሮ ማስኬድ አለበት ብለዉ የግብርና ባለሙያተኞች ድጋፍ የየእለት ተግባራቸዉ አድርገዉ አርሶአደሩን ምርት ሳይባክን የሚሰበስብበት ሂደት መፍጠር እንዳለባቸዉም አመላክተዋል።

በወረዳዉ በበልግ የምርት ወቅት ድንችና የበቆሎ ምርት ላይ በስፋት እየተሰራጨ እንደሆነም አስታዉቀዉ የድንች ምርት አሰባሰብ ስራዉ ቀደም ተብሎ የተጀመረ እንደሆነና በተለያዩ ቀበሌዎች ድንች በማህበር ተደራጅተዉ የሚያመርቱ አርሶአደሮች እንዳሉና የነዚህም ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

በበልግ ወቅት 4 ሺህ 3 መቶ 80 ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች የተሸፈኑ መሆኑም አስታዉሰዉ ምርትም እየተነሳ እንደሆነም ጠቁመዉ በመኸር የተዘሩ ያልደረሱ ማሳዎች አርሶአደሩ የሰብል በሽታና የተባይ ቁጥጥር ስራዉ በመከታተልና የማሳ እንክብካቤዉን ስራ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አሳስበዋል።

ምርት የማከማቻ ጎተራዎች ከተባይና መሰል በሽታዎች በጸዳ መልኩ በማዘጋጀት የሚፈለገዉን የምግብ ዋስትና በዘላቂነት ማረጋገጥ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የአየር ሁኔታዉ ተለዋዋጭ በመሆኑ አርሶአደሩ ሳይዘናጋ የደረሱ ሰብሎች ማንሳት እንዳለበትም አሳስበዋል።

በወረዳዉ ቀጣነ ቀበሌ ያነጋርናቸዉ አርሶአደር ይትባረክ ተክለማሪያም እና አርሶአደር ክብሩ ስባኒ በሰጡት አስተያየት በማሳቸዉ ገብስ ፣ ባቄላና የመሳሰሉት ሰብሎች መዝራታቸዉ ጠቁመዉ በዚህም የሚፈልጉትን ምርት ለማግኘት የአንድ ለአምስትና የአንድ ለአስር አደረጃጀቶችን በመጠቀም እየሰሩ እንደሆነም ጠቁመዋል።

አክለዉም አርሶአደሮቹ በኩታ ገጠም ሙሉ ፓኬጅ ተጠቅመዉ በማረስ ዉጤታማ እንሚሆኑም አመላክተዋል ሲል የዘገበዉ የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነዉ።

በተጨማሪም እነዚህ ሊንኮችን በመጫን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡
Facebook:- https://www.facebook.com/gurage1Zone
Website:- https://gurage.gov.et
Telegram:- https://t.me/comminuca
Youtub: -https://www.youtube.com/channel/UCzrcazGvvIO2tG7bQN36Cx

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *