ምርትና ምርታማነትን ለማረጋገጥና ድህነትን ታሪክ ለማድረግ በሚደረገው ሂደት እንቅፋት የሚሆኑ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጡ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሀላፊ አቶ ተመስገን ካሳ ጠየቁ።

በጉራጌ ዞን አበሽጌ ወረዳ በዋልጋ ከተማና በአጎራባች ቀበሌዎች ከሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በሰላም ዙሪያ ውይይት ተደርጓል።

በውይይቱ ወቅት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሀላፊ አቶ ተመስገን ካሳ እንደገለጹት የወረዳውን መገለጫ የሆነው ምርትና ምርታማነትን ለማረጋገጥና ድህነትን ታሪክ ለማድረግ በሚደረገው ሂደት እንቅፋት የሚሆኑ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጡ አሳስበዋል።

ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት በመሆኑ ሁላችንም ልንጠብቀው እንደሚገባ ገልፀው በወረዳው የሰላም ችግር ባለባቸው ቀበሌዎች በየደረጃው ከህዝቡ ጋር ውይይት እተደረገ መሆኑንና ለህብረተሰቡ ስጋት በሚሆኑ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።

የክልሉ መንግስት የሰላም ችግር ባለባቸው አካባቢዎች በየደረጃው ከህዝቡ ጋር ውይይት እያደረገ መሆኑን ገልጸው ለህብረተሰቡ ስጋት በሚሆኑ አካላት ላይ የህግ ማስከበር እርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቀዋል።

በአበሽጌ ወረዳ ዋልጋ ከተማና አካባቢው ላይ ያለው የሰላም ችግር ለመፍታት ህብረተሰቡ ከመንግስት ጋር በመሆን አጥፊዎች ከችግራቸው እንዲቆጠቡና እጃቸውን ለመንግስት በመስጠት ወደ ሰላማዊ ኑሮአቸው እንዲመለሱ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

የጉራጌ ዞን ሰላምና ጸጥታ መመምሪያ ሀላፊ አቶ የህያ ሱልጣን በበኩላቸው ህብረተሰቡ በየትኛውም አደረጃጀትና እንቅስቃሴ ከመንግስት አካላት ጋር በመሆን ሰላም የሚያውኩ አካላትን አሳልፎ መስጠት እንዳለበት ጠይቀዋል።

ሰላም ለማስፈን በተለያዩ ጊዜያት በሚፈጠሩ መድረኮች ከህዝቡ ጋር መግባባት ላይ እየተደረስ መሆኑን ገልፀው የህዝቡን ሰላማዊ ኑሮን የሚያውኩ አካላት ስጋት የማይሆኑበት ደረጃ ላይ ለማድረስ እንደሚሰራ አስረድተዋል።

ጠላታችን ድህነት መሆኑን ተገንዝበን በልማት ስራዎች ላይ በማተኮር ለግል ጥቅማቸው ሲሉ የብሔር ታርጋ በመለጠፍ በእኩይ ተግባር የተሰማሩ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ በአፅንኦት አሳስበዋል።

የአበሽጌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ካሱ ጁሀር በበኩላቸው የወረዳው ህዝብ ፍላጎት በሰላም መኖርና ምርታማነትን ለማሳደግ የግብአት ጥያቄ መሆኑን ገልጸው ለዚህም ወረዳው የአርሶ አደሩን ፍላጎት ለማሟላት አስፈላጊውን ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

የግል ፍላጎታቸውን ለማሟላት ተዋዶና ተፋቅሮ የሚኖረውን ህዝብ የሚያውኩ አካላት መኖራቸውን ገልጸው ምርትና ምርታማነት የሚረጋገጠው ሰላም ሲሰፍን በመሆኑ በዋልጋ መዘጋጃና አካባቢው እየተስተዋለ ያለው የጸጥታ ችግር በውይይት ለመፍታት አንደኛው አማራጭ መሆኑን ገልጸዋል።

በአካባቢው ለረጅም ጊዜ ተቻችሎ በኖረ ህዝብ መሀል ላይ የሰላም ችግር እየፈጠሩ ያሉ አካላት ማህበረሰቡ ውስጥ ተሸሽገው ያሉ በመሆናቸው ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡና ማህበረሰቡም እነዚህ አጥፊዎች መምከርና ከችግራቸው በማይታረሙት ላይ ያለ አደርባይነት ለመንግሥት መረጃ መስጠት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ወረዳው ከኦሮሚያ ክልል ከሚዋሰኑ ወረዳዎች ላይ ሰላም እንዲሰፍን ጥሩ ውይይቶች በማካሄድ ላይ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።

የመደረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው መንግስት የህግ የበላይነት እንዲያስከብርላቸው በመጠየቅ
የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች አቅርበው በመድረኩ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።

በውይይቱ ዋልጋ ከተማ ፣ ናቻ ከተማ ፣ፊቴ ጀጁ ቀበሌ ፣ሚዳ ቀበሌ ፣ቦረር ቀበሌና ናቻ ገጠር ተሳታፊ ነበሩ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *