ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ እንዳሻው ጣሰው የጉራጌ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ ግንባታ ላይ የበኩሉን ደማቅ አሻራ ያሳረፈና ዛሬም ሚናውን እየተወጣ የሚገኝ የትጋትና የአብሮነት ተምሳሌት የሆነ ህዝብ ነው አሉ።
ክቡር ፕሬዚዳንቱ ፣ከፍተኛ የክልሉ አመራሮችና የጉራጌ ዞን የህብረተሰብ ተወካዮች ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሞቀ አቀባበል በወልቂጤ ከተማ አድርገዋል።
አቶ እንዳሻው ጣሰው በወልቂጤ ከተማ ስታዲየም ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና በስታዲየሙ ለተገኘው ህዝብ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ክቡር ፕሬዚዳንቱ ባስተላለፉት መልዕክት የጉራጌ ማህበረሰብ ከትውልድ ወደትውልድ ሲሸጋገሩ በዘለቁ የሰላም ግንባታ እሴቶች እየተጋዘ፣ ለዘላቂ ሰላምና ልማት ግንባታ የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።
የጉራጌ ማህበረሰብ ከሌሎች እህትና ወንድም ኢትዮጵያውያን ጋር በመተባበር በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና በማህበራዊ ግንባታ መስኮች ደማቅ ታሪክ መጻፉንም አቶ እንዳሻው አመልክተዋል።
ፕሬዚዳንቱ አክለውም የጉራጌ ማህበረሰብ በህብረተሰባዊ የለውጥ ሂደት አመክንዮ የሚስማማ፣ለአመክንዮ መርሆዎች የሚገዛና ሰርቶ ለመለወጥ ተምሳሌታዊ ስብዕና የተላበሰ መሆኑንም አሳውቀዋል።
የጉራጌ ማህበረሰብ ከሌሎች ለውጥ ፈላጊ ኢትዮጵያውያን ጋር በመቀናጀት ለውጡ እንዲሳካና የሪፎርም ስራዎች እንዲሳለጡ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉንም ጠቁመዋል።
አሁንም የተጀመሩ ሁሉ አቀፍ ጥረቶች እንዲሳኩ ማህበረሰቡ የላቀ ጥረትና ርብርብ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።