መኸር ከሚለማው በተጨማሪ ስንዴን ወቅቱን የጠበቀና የሀገሪቷን ነባራዊ ሁኔታ የሚመጥን በበጋው መስኖ መልማት እንዳለበት የጉራጌ ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡

በዛሬው እለት በጉራጌ ዞን በአበሽጌ ወረዳ በናቻ ቁሊት ቀበሌ በመስኖ የሚለማ የስንዴ ዘር የማስጀመሪያ ዝግጅት የዞንና የወረዳ ከፍተኛ አመራሮች፣አርሶ አደሮችና ባለሞያዎች በተገኙበት ተካሄዷል፡፡

በዝግጅቱ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የጉራጌ ዞን የመንግሰት ዋና ተጠሪ የሆኑት አቶ ክፍሌ ለማ እንደገለጹት በዚህ በሰላማዊ ቦታ አንዱ የጦር ግንባር የሆነው ግብርናችንና ማሳችን ላይ መንግስት ላቀረበው ጥሪ ምላሽ ለመስጠት ሁሉም ትኩረት መስጠት አለበት ብለዋል፡፡

በተጨማሪም በሰሜኑ የሀገራችን በጦርነት ምክንያት አርሶ አደሩ ምርት እንዳላመረተና የተመረተውም ምርት የጥፋት ቡድኑ እየዘረፈና እያቀጠለው ስለሆነ ከውጭ መንግስት በድጎማ የሚያስገባውም ስንዴ የጥፋት ቡድኑን በሚደግፉት ምእራባዊያን ምክንያት እየተስተጓጎለ እንደሆነም አብራርተዋል፡፡

አክለውም ሀገራችን ቀድሞም የምግብ ዋስተና ችግር የነበረባት ስለሆነች ወደ ባሰ ችግር ውስጥ እንዳትገባ በሀገር ውስጥ ምርታችን፣ በሀገር ውስጥ ሀይላችን አስተባብረን አጽንኦት ተሰቶ መሰራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

እንደ ዞን 2 ሺ 1 መቶ ሄክታር መሬት በላይ በበጋው መስኖ ስንዴን ለማልማት እንደታቀደና ይህንንም ለማሳካት በተላያዩ የዞኑ ወረዳዎች እንደተጀመረ የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ ተናግረዋል፡፡

አክለውም በመኸር ከሚለማው በተጨማሪ ስንዴን ወቅቱን የጠበቀና የሀገሪቷን ነባራዊ ሁኔታ የሚመጥን በበጋው መስኖ ማልማት ጉዳይ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ እንደሆነም አስረድተዋል ፡፡

አያይዘውም ማዳበሪያና ምርጥ ዘር እንዲሁም የተለያዩ የግብርና ግበአቶችንም ጭምር ክልሉ እንደሚሸፍን ጠቁመው ዕቅዱንም ለማሳካት የአመራርና የባለሞያ ዝግጅት ከፍተኛ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በጉራጌ ዞን የአበሽጌ ወረዳ አስተዳድሪ አቶ መላኩ ብረሀኔ እንደገለጹት መንግስት ባስቀመጠው እቅድ መሰረት የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመቋቋም ስንዴን በበጋው መስኖ የማልማቱ ስራ መጀመሩን ገልጸው ፤መሪያችንና ወጣቱ በሀገር ህልውና ዘመቻው ላይ በግንባር እየተሳተፈ መሆኑን አውስተው አርሶ አደሩ ደግሞ በግብርናው ዘርፍ መዋጋት አለበት ብለዋል፡፡

በበጋው በመስኖ የሚለማው ስንዴ ስራው በጣም አዋጭ መሆኑን አርሶ አደሩ ተረድቶ በግልም ፣በማህበርም በመደራጀት ያሉትን ጅኔሬተሮችና ፓንፖች በመጠቀም መረባረብ እንዳለበት አብራርተዋል፡፡

እንደ ሀገር ብሎም እንደዞን የታቀዱ እቅዶች ወደ ወረዳችን አቅም በመቀየር በወረዳችን 1 መቶ 97 ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት በተለያዩ የወረዳው ቀበሌዎች መጀመሩን የወረዳው ም/ አስተዳዳሪና የግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዘመተ አይፎክሩ ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም 8 ሺ 3 መቶ 20 ሄክታር መሬት በመደበኛ መስኖ በተለያዩ ሰብሎችና አትክልቶች በመስኖ ለመሸፈን መታቀዱንና ስራው መጀመሩን ተናግረው ፤ለስንዴዉም ዘር የማሳ ዝግጅት ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ወደ ተግባር መገባቱን አስረድተዋል፡፡

ካነጋገርናቸው ባለሙያዎች መካከል አቶ ያለው አሰፋ የወረዳው በግብርናው ዘርፍ የሄክስቴሽን ባለሞያ ሲሆን በናቻ ቁሊት ቀበሌ ለአርሶ አደሮቹ አዳዲስ ቴክኒሎጅዎችና የግብርና ግበአት አጠቃቀምና ሌሎች ሞያዊ ድጋፎችን እያደረገ እንደሚገኝ ገለፆ በቀጣይም ሙያዊ ሀላፊነቱን በተገቢ እንደሚወጣ ገለፀዋል፡፡

ካነጋገርናቸው አርሶ አደሮች መካከል አቶ ሳሙኤል ሄራሞ እና አቶ መለሰ ሀይሌ ሁለቱም በሰጡት አስተያየት ይህ በመስኖ የሚለማው ስንዴ በቀበሌያቸው አዲስ መሆኑንና ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ መንግስት እንዲዘሩ ድጋፍ ማድጉ እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል፡፡በተጨማሪም በትኩረት ለመስራት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *