መስቀል_በጉራጌ

መስከረም10/2015 ዓ.ም

መስቀል_በጉራጌ

የመስቀል በዓል ከአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ማለትም ንግሥት እሌኒ ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበትን መስቀል አስቆፍራ ካስወጣችበት ጊዜ ጀምሮ በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ይከበራል፡፡

ንግሥቲቷ መስቀሉ የተቀበረበትን ቦታ ቂራቆስ በተባሉ አባት ጠቋሚነት ለማግኘት ደመራ አስደምራ ፍለጋ የጀመረችው መስከረም 17 ቀን እንደሆነ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡

የሃይማኖት አባቶችን አሰባስባ በፀሎት እንዲረዷት ጠይቃ፣ ከደመራው በሚወጣው ጢስ ጠቋሚነት መስቀሉ የተቀበረበትን ቦታ አግኝታለች፡፡ መስቀሉም ከወራት ቁፋሮ በኋላ ወጥቷል፡፡ ከዚያን ወቅት ጀምሮ መስከረም 16 ቀን የደመራ ሥነ ሥርዓትና መስከረም 17 የመስቀል በዓል ይከበራል፡፡

የመስቀል በዓል ሃይማኖታዊ ይዘቱ እንዳለ ሆኖ በየአካባቢው እንደየማኅበረሰቡ ባህልና ወግም ይከበራል፡፡ ከሌሎች ዐውደ ዓመቶች የመስቀል በዓል በተለየ በድምቀት በሚከበርባቸው አካባቢዎች የብዙ ጎብኚዎችን ትኩረትም ይስባል፡፡ በዓሉ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የማይዳሰሱ ቅርሶች መዝገብ ላይ በዓለም ቅርስነት የሰፈረውም ለዚሁ ነው፡፡

በጉራጌ ብሔረሰብ ዘንድ በድምቀት ከሚከበሩ በዓላት መካከል ትልቁና ዋንኛው የመስቀል በዓል ነው፡፡ የመስቀል በዓል በጉራጌ ብሔረሰብ ያለው ማህበራዊ ፋይዳ ዓመቱን ሙሉ ተለያይተው የኖሩ ቤተሠቦችና ዘመዳሞች የሚገናኙበት፣ የሚጠያየቁበት፣ ማህበራዊ ችግሮቻቸው የሚፈቱበት፣ ወጣቶች የሚተጫጩበት፣ በጋብቻ የተሳሰሩ ቤተሠቦች የሚጠያየቁበት፣ የተጣሉ ሠዎች የሚታረቁበት፣ እዳ የሚሠረዝበትና በዳይና ተበዳይ ይቅር የሚባባሉበት በዓል ነው፡፡

መስቀል በጉራጌዎች ዘንድ በተለየ ሁኔታ የሚከበረው ለበዓሉ የተለየ ፍቅርና ከበሬታ ስላላቸው ነው። ከዚህም የተነሳ ከመላው ኢትዮጵያና ከተለያዩ ሀገሮች ጭምር ተወላጆቹ በመስቀል ሰሞን በነቂስ ወደ ትውልድ መንደራቸው ይተማሉ፡፡

የጉራጌ ልጆች በህይወት እያሉ ችግር ካልገጠማቸው በቀር የገንዘብ አቅም ማነስ ቢፈታተናቸው እንኳን ተበድረውም ቢሆን ለመስቀል ወደ ወላጆቻቸው ከመሄድ አይቀሩም። ምክንያቱም እናትና አባት፣ ቤተሰብና ጎረቤታቸው በናፍቆት ይጠብቋቸዋል።

በዓሉን ከቤተሰባቸው ጋር በማክበራቸው ምርቃትና በረከትን ይቀበላሉ። በበዓሉ ወቅት ሊስትሮ ጠራጊ፣ ቅርጫት ተሸካሚው፣ ጉሊት ቸርቻሪዎች፣ ሱቅ በደረቴዎች፣ የሰው ቤት ሰራተኞች፣ የሻይ ቤትና የሆቴል አስተናጋጆች፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ነጋዴዎች፣ ከፍተኛ ባለኮከብ ሆቴል ባለቤቶች፣ የአምራች ኢንዱስትሪ ባለሀብቶች ለመስቀል ሀገር ቤት ይገባሉ።
በመስቀል ሰሞን አዲስ አበባና ሌሎች በርካታ የሀገራችን ከተሞች ቀዝቀዝ ያለ ድባብ ይታይባቸዋል፡፡
#የመስቀልበዓልዝግጅት
የጉራጌዎች የመስቀል በዓል አከባበር ከወረዳ ወረዳ በአንዳንድ ክንዋኔዎች ላይ በጣም መጠነኛ ልዩነቶች ቢኖሩትም አጠቃላይ ባህርዩ ግን ተመሳሳይ ነው። መስቀል በጉራጌ ብሔረሠብ ዘንድ ትልቅ በዓል እንደመሆኑ መጠን ዝግጅቱም እንዲሁ ከበድ ያለ ነው፡፡

የመስቀል በዓል ዝግጅት የሚጀምረው መስቀል በተከበረበት ማግስት ጀምሮ ለሚቀጥለው አከባበር ማሠብ ይጀመራል፡፡
መስቀል ሶስትና አራት ወራት ገደማ ሲቀሩት ዝግጅቱ እየተጧጧፈ ይሄዳል፡፡ በዚህ ወቅት የሥራ ክፍፍሉ በዕድሜና በፆታ እንደየ አቅሙና ችሎታው ይሠጣል፡፡
አባት በወንድ ልጆቹ እየታገዘ በበጋው ወቅት ለመስቀል የሚሆን በቂ የማገዶ እንጨት ያዘጋጃል። ቤቱ አርጅቶ ከሆነ ይጠግናል። በዓሉ ሲቃረብም በከተሞች ከሚኖሩ ልጆቹና ወንድሞቹ በሚላክለት ገንዘብ ካለዚያም በራሱ ወጭ የመስቀል የእርድ ከብት ይገዛል።

እናት ደግሞ በሴት ልጆቿ እየታገዘች ለመስቀል የሚያስፈልገውን ቆጮ፣ ቅቤ፣ ቡላ፣ አይብ፣ ጎመን፣ ሚጥሚጣ፣ ቅመማቅመሞች ታዘጋጃለች። ሴት ልጆች ቤቱንና ደጁን ያሳምራሉ። ግድግዳውን የባህል ቀለም በጥብጠው በማዘጋጀት ይቀባሉ።

መስቀል በጉራጌ አስቀድሞ ሰፊ ቅድመ ዝግጅት ከተደረገበት በኃላ በዓሉ ከመስከረም 12 እስከ ጥቅምት 5 ድረስ ለበዓሉ ተብሎ የተዘጋጀ ባህላዊ ምግቦችና መጠጦች እየተጠቀሙ በታላቅ ደስታና ጭፈራ እንዲሁም ልዩ ልዩ ክንዋኔዎችን በማካሄድ የሚከበረ ሲሆን የቀናቶቹ ስያሜና የሚካሄዱ ተግባራት እንደሚከተለው ይሆናል፡፡

   #መስከረም_13_ወሬት_የኸና

በመስቀል በዓል ለምግብ ማቅረቢያነት የሚውሉ ቁሳቁሶች ከየግድግዳው የሚወርዱበት ቀን ነው፡፡ የቤት መገልገያ ቁሳቁሶች በጥንቃቄ ፀድተው እስከ ጥቅምት 5 ድረስ በምግብ ማቅረቢያነት ያገለግላሉ፡፡

በተጨማሪያም ሁሉም ቤቱን አፅድቶ አዳዲስ ጅባዎች አነጣጥፎ መስቀልን ለማክበር ዝግጅት የሚጠናቀቅበት ዕለት ነው፡፡

መስከረም 14 ደንጌሳት /የዴጚያ እሳት(ይፍት)
ለሁሉም የቤተሰብ አባል በተዘጋጀለት የሸክላ ጣባት የጐመን ክትፎ የሚበላበት ቀን ነው፡፡ የዚህ ቀን ሙሉ ወጪ የሚሸፍኑት ሴቶች ናቸው፡፡ በዚህ ዕለት ማታ በየደጃፉ በልጆች የተደመሩ ዳመራዎች የሚቃጠሉበት ቀን ሲሆን በብሔረሰቡ አጠራር የዴጚያ ኧሳት (የባዮች ኧሳት ቀነ) ይባላል፡፡

ስለሆነም ዳመራው ሲቃጠል ጎረ ጎረ ፣ ጎረ ጎረ… እያሉ ፈጣሪን ለዚህ እለት ላደረስከን ብለው ሲያመሰግኑ ሴቶች ደግሞ በእልልታ ያደምቁታል፡፡

መስከረም 15 ወኸመያ /ጨርቆስ/ የእርድ ማይ/
በጉራጌ ማህበረሰብ የመስቀል ክብረ-በዓል የእርድ ስነ- ስርዓት የሚከናወነው በአመዛኙ መስከረም 15 ነው።

ይህ ዕለት ወኸምያ ይባላል። በዚህ ዕለት ዝቅተኛም፣ መካከለኛም ሆነ የተሻለ ኑሮ ያለው የጉራጌ ተወላጅ በየደጁ የእርድ ስነ-ስርዓት ያከናውናል።

የሚታረደው ከጥጃ እስከሰንጋ ሲሆን የእርድ ከብቱን ደረጃ የሚወስነው አንድም የቤተሰቡ የኢኮኖሚ አቅም ሌላውም የቤተሰቡ አባላት ብዛት ነው። አንድ ከብት ለብቻው፣ ለሁለት ወይንም ለአራት ቤተሰብ በጋራ ታርዶ ሊከፋፈል ይችላል።

እዚህ ላይ ሊነሳ የሚገባው ቁምነገር የማህበረሰቡ የመተሳሰብ፣ የመከባበር፣ ተፈቃቅሮ አብሮ የመኖር ትልቅ እሴት ነው። ይኸውም በሰፈሩ ውስጥ ልጆች የሌሉት ወይንም ያልደረሱለት፣ የእርድ ከብት ሊገዛለት የሚችል ምንም ዓይነት ዘመድ በከተማ የሌለው፣ የኢኮኖሚ አቅሙ በጣም ደካማ የሆነ ቤተሰብ በመንደሩ ውስጥ ካለ የተሻለ አቅም ያላቸው ቤተሰቦች “እኛ አርደን ስንበላ እነርሱ በበዓል ጦም ማደር የለባቸውም” በሚል በጎ ስሜት ከታረደው ከብት ድርሻቸው ላይ በማንሳት የተወሰነ ስጋ አቅሙ ደካማ ለሆነው ቤተሰብ ይሰጣሉ።

መስከረም 16 ያባንዳ እሳት/ የጉርዝ እሳት
ዋናው መስቀልና ትልቁ /የአባቶች/ ዳመራ የሚበራበት ዕለት ሲሆን በአብዛኛው ሀይማኖታዊ ይዘት ይላበሳል፡፡ ወጣት ወንዶችና ሴቶች ቤተክርስቲያን ሄደው ባህላዊ ጭፈራ <<አዳብና>> የሚጨፍሩበትና ሀይማኖታዊ ሥርዓት
የተከተለ ዳመራ የሚቃጠልበት ቀን ነው፡፡በዚህ እለት የሚከናወነው የደመራ ስነስርዓት (ይሳት ከረ) የክርስትና እምነት ተከታይ በሆኑ ጉራጌዎች ዘንድ ልክ እንደ እርድ ስነ-ስርዓት ሁሉ የተለየ ክንዋኔ አለው። ጠዋት በቅቤ የተዘጋጀ ጣፋጭ የቡላ ገንፎ (ያጥሜጥ ኦዛት) ይባላል። ከዚያም የቅቤ ቡና (የቅብ ቃዋ) ይጠጣል።

መሰንበቻውን በየአብያተ-ክርስትያናቱ ደጃፍ በአካባቢው ወጣቶች የተደመረው የአድባራት የደመራ ማህበራት ስነ- ስርዓት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ስርዓት በሚፈቅደው መሰረት ከቀትር በኋላ በድምቀት ይከናወናል። ምሽቱን ሁሉም ሰው በየደጁ (ጀፎረ) ላይ ማምሻውን ችቦ ያበራል።

መስከረም 17 ንቅ ባር/ የከሠል ማይ
ከለሊቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በአንድ አጥቢያ የሚተዳደሩ ዕድርተኞች ዳመራ ወደ ተቃጠለበት ቦታ በመሰብሰብ ቃለ መሀላ በማስገባት አዲስ የአካባቢ ዳኛ የሚሾምበትና ያለፈው ርክክብ የሚያደርግበት፣ አዲስ የአባልነት ጥያቄ የሚቀርብበትና ምዘግባ የሚካሔድበት ዕለት ነው፡፡

  መስከረም 18 የፊቃቆማይ

ሴት ልጃገረዶች የተለያዩ የሥፌት ጌጣ ጌጦች /ዕቃዎች/ ለማዘጋጀት የሚረዳ ሰንደዶ ለቀማ የሚጀመርበት ዕለት ሲሆን በየመንደሩ ልጃገረዶች ባህላዊ ዜማ እያዜሙ ሰንደዶ ለቀማ ያደርጋሉ፡፡

ከመስከረም 17 እስከ መስከረም 23 <<የጀወጀ/ የጀወቸ>>
አማትና አማች የመጠየቂያ ጊዜ ነው፡፡ ሴት ልጆች ለእናቶቻቸው የፀጉር ቅቤ ለአባቶቻቸው ባርኔጣና ጭራ ሲይዙ ባሎቻቸው ደግሞ ሙክት በመያዝ ይሄዳሉ፡፡ ራሳቸው የአብራካቸው ክፋይ የሆኑትም ልጆቻቸው በወላጆቻቸው የሚመረቁ ሲሆን በጠቅላላ አማቾቻቸው ዘንድ ትልቅ ክብርና ሞገስ ያጐናፅፏቸዋል፡፡

ባህለዊ የመስቀለ በዓል ጨዋታ <<አዳብና>> አዳብና ከመስቀል በዓል ጋር ተያይዞ ከመስከረም 16 እስከ ጥቅምት 5 ባሉት ቀናት ውስጥ በተለያዩ የገበያ ቦታዎችና አቢያተ-ክርስቲያናት የሚከወን የወጣቶች ባህላዊ ጭፈራ ስነ- ስርዓት ነው፡፡

በዚህ ሰነ- ስርዓት ላይ በተለያዩ ምክንያቶች ከየትውልድ ቀዬያቸው ርቀው የቆዩ ዘመድ አዝማዶች፣ አብሮ አደጐች ተገናኝተው ናፍቆታቸው ይወጣሉ፡ የሠውም ሆነ የጥበብ ናፍቆት፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ክብ እየሰሩ የሚዘፍኑ ወጣት ወንዶችና ሴቶች ዜማና ዳንኪራ በሚደምቀው በዚሁ የአዳብና ጭፈራ ወቅት የትዳር ጓደኛ የመምረጥ ስራ ይከናወናል፡፡ ወንዱ ልጅ ለጭፈራ ከወጡት ኮረዳዎች መሀከል ቀልቡ ካረፈባት ልጅ የሎሚ ስጦታ በመስጠት /ወርውሮ/ በመምታት ለትዳር የምትሆነውን ልጅ በባህሉ መሠረት ያጫል፡፡

በአጠቃላይ በመስቀል ወቅት የሚከናወኑ ባህላዊ መስተጋብሮችና ትዕይንት ለዞኑ ቱሪዝም እድገት ትልቅ ሀብት ነው፡፡ በዞኑ በአለም ቅርስነት ከተመዘገበው ጢያ ትክል ድንጋይ ጀምሮ የጊቤ ሸለቆ ብሔራዊ ፖርክ፣ ጥንታዊና ታሪካዊ ገዳማትና መስጅዶች እንደሁም ውብና ማራኪ የሆኑ መልክአ ምድሮችን የያዘውን ጉራጌ ዞን የመጐብኘት አድል ይፈጥራል፡፡ በባህላዊ እንግዳ አቀባበልና በመስቀል በዓል አከባበራችን ተደስተው በዞኑ በሚገኙ ብሔረሰቦች ባህል፣ ታሪክ፣ ወግና በተፈጥሮ ሀብቶችዋ ረክተው ይመለሳሉና እንዲጎበኙ ጋብዘንዎታል፡፡
መልካም የመስቀል በዓል!!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *