ለግብር ከፋዩ ማህበረሰብ የዘመነ አገልግሎት በመስጠት ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ ለመሰብሰብ እየሰራ እንደሚገኝ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ።


ለግብር ከፋዩ ማህበረሰብ የዘመነ አገልግሎት በመስጠት ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ ለመሰብሰብ እየሰራ እንደሚገኝ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው ከፌዴራል ገቢዎች ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ለደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች በኢ-ታክስ እና ኢ-ፋይሊንግ አተገባበር ላይ የአሰልጣኞች ስልጠና በወልቂጤ ከተማ ተሰጥቷል።

የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ምክትል እና የደንበኞች አገልግሎት የታክስ አወሳሰን እና አሰባሰብ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ደግፍ መለሰ እንደገለፁት ቢሮው የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ለማሻሻል ግብር ከፋዩ ማህበረሰብ ባለበት ሆኖ ግብሩን የሚያሳውቅበትና የሚከፍልበት የኢ-ታክስ ሲስተም ለማስፋፋት እየተሰራ ይገኛል።

የኢታክስ ሲስተም ማስፋፋት ግብር ከፋዩ ማህበረሰብ ካላስፈላጊ ወጪ፣ ጊዜና ጉልበት የሚታደግ ብቻ ሳይሆን ደንበኞች በተቋሙ ላይ ያላቸው እምነት ከፍ እንዲል ያደርጋል።

ይህንን አገልግሎት ስኬታማ ለማድረግ ሰልጣኞች የግብር ከፋይ ደንበኞች መረጃ በአግባቡ በማደራጀት ከዚህ ቀደም ይቀርቡ የነበሩ ችግሮች በመሰረታዊነት እንዲቀረፉ በቁርጠኝነት መስራት እንደሚጠበቅባቸው አቶ ደግፍ አስገንዝበዋል።

ደንበኞች የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲያገኙ ቢሮው ግብ ጥሎ እየሰራ እንደሚገኝ የገለፁት ኃላፊው በሚቀጥለው በጀት አመት ግብር ከፋዮች ሳይጉላሉ ባሉበት ሆነው በኢ ታክስ ሲስተም እንዲገለገሉ ለማድረግ ባለሙያዎች ከወዲሁ ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

ክልሉ የሚያመነጨው ሀብት አሟጦ ለመሰብሰብ የተቋሙ የሰው ኃይል ለማበቃት ስልጠናው ትልቅ አቅም ይፈጥራል ነው ያሉት አቶ ደግፍ።

የኢ- ታክስ እና የኢ ፋይሊንግ አገልግሎት የክልሉ ግብር ከፋዮች በራስ ተነሳሽነት እና የኔነት ስሜት ግብርን በወቅቱ እና በታማኝነት እንዲከፍሉ የሚያስችል በመሆኑ ደንበኞች የጠራ መረጃዎች ማቅረብ እንደሚጠበቅባቸው አስረድተዋል።

እንደ አቶ ደግፍ ገለፃ የፌዴራል ገቢዎች ሚኒስቴር የክልሉ ገቢዎች ቢሮ የሰው ሀይል አቅም ለመገንባት አሰልጣኝ በመመደብ ለሰጠው ስልጠና ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በፌደራል ገቢዎች ሚኒስቴር የታክስ ስርዓት ማጣጣምና የክልሎች ድጋፍ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መሀመድ ሀሶ በበኩላቸው በሀገሪቱ የኢ-ታክስ ሲስተም በተጀመረባቸው ክልሎች ከፍተኛ ውጤት ያስገኘላቸው አሰራር በመሆኑ ሲስተሙ ባልተጀመረባቸው ክልሎች ለማስፋፋት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

ከዚህ ቀደም ይሰራበት የነበረው ማንዋል የታክስ አከፋፈል ስርዓት ወደ ዲጂታል በመለወጥ ግብርከፋዮች ወደ ገቢ ተቋም ሳይመጡ ባሉበት የስራ አካባቢ ግብራቸውን አሳውቀው መክፈል የሚችሉበት፣ አቤቱታ የሚገልፁበት፣ ክሊራንስ የሚወስዱበት ሲስተም መሆኑን ተናግረዋል።

በስልጠናው ላይ ያገኘናቸው በወልቂጤ ከተማ ገቢዎች ጽ/ቤት የደንበኞች አገልግሎት የታክስ አወሳሰን አሰባሰብ ዳይሬክቶሬት አስተባባሪ ወይዘሮ አየለች ስፍር እና ከቡታጅራ ከተማ ገቢዎች ጽ/ቤት የደንበኞች አገልግሎት የታክስ አወሳሰን አሰባሰብ ዳይሬክቶሬት አስተባባሪ አቶ በለጠ ገዳ እንደገለፁት የታክስ አሰባሰብ ስርዓት ለማዘመንና አገልግሎትን ለማቀላጠፍ ያስችላል ብለዋል።

ቴክኖሎጂው ጊዜ፣ ጉልበትና ወጪ ቆጣቢ መሆኑን የገለጹት ሰልጠሰኞቹ ቴክኖሎጂው ወደ ተግባር ሲገባ የገቢ ተቋም ባለሙያዎች የስራ ጫና እና የደንበኞች እንግልት ይቀንሳል ብለዋል።

በመሆኑም በስልጠናው ያገኙትን እውቀት በመጠቀም ስራዎቻቸው ለማዘመን በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *