ለወልቂጤ ከተማ ልማት ፣እድገትና በከተማዉ ገጽታ ግንባታ ባለሀብቱ ፣ ነጋዴዉና መላዉ የከተማው ህዝብ ሊያግዝ እንደሚገባ የወልቂጤ ከተማ ከንቲባ ጥሪ አቀረቡ።

ከተማ አስተዳደሩ ከነጋዴዉ ማህበረሰብ ጋር በንግድ ግብር ክፍያ በከተማዉ መልሶ ማልማት፣ በሰላምና በመልካም አስተዳደር ዙሪያ የምክክር መድረክ ተካሄዷል።
የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ እንዳለ ስጦታዉ በምክክር መድረኩ እንዳሉት በከተማዉ የመልማት ጉዳይ ላይ በቅድሚያ አስተሳሰብ መቀየር እንዳለበትና ዜጎች በሰላም ወጥተዉ እንዲገቡ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ይገባል።

በከተማዉ ልማት ፣እድገትና በከተማዉ ገጽታ ግንባታ እንዲሁም ባለሀብቱ ፣ ነጋዴዉና መላዉ ህዝብ ሊያግዝ እንደሚገባና የህግ የበላይነት እንዲሰፍን በማድረግ ከገጽታዉ አካላት ጋር ተቀናጅቶ መስራት እንደሚገባም አብራርተዋል።

ለከተማዉ እድገትና ልማት እንቅፋት እየሆኑ ያሉ በመንግስት መዋቅር ዉስጥ የተሸሽጉ ህገወጦች በተገቢዉ የማጥራት ስራ እንደሚሰራም አስረድተዋል።

ከተማዉ ዉስጥ ሁሉም ብሔሮች እኩል እንደሆኑና በሰላም ፣በልማት እኩል ተሳታፊ መሆን እንዳለባቸዉም አንስተዉ ሁሉም በመተጋገዝ ወልቂጤ ከተማ ላይ ለዉጥ ማምጣት እንደሚቻል አብራርተዋል።

በከተማዉ የገጽታ ግንባታ ላይ ያሉ የመንግስት ቤቶች ህግና ስርአት በተከተለ መልኩ በጨረታ የሚሸጡ እንደሆነም ጠቁመዉ በዚህም በከተማዉ ዉስጥ ያሉ ባለሀብቶች ህብረተሰቡ የበኩላቸውን ማገዝ ይኖርባቸዋል።

በከተማዉ የንጹሁ መጠጥ ዉሃ ችግር ለመቅረፍ የተጀመሩ ስራዎች መኖራቸዉም ተናግረዉ በዚህም የሁሉም ሰዉ ድጋፍና ርብርብ እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል።

የከተማዉ የንጹህ መጠጥ ዉሃ ችግር ሙሉ ለሙሉ እስኪቀረፍ በሬቡ እና በቦዠባር የንጹህ ዉሃ መጠጥ ወሃ በህገ ወጥ መንገድ የሚጠቀሙትን በማስቆም እንደማንኛዉም ማህበረሰብ በፈረቃ እንዲጠቀሙ ለማድረግ ይሰራል ብለዋል።
የጣጤሳ ዉሃ መስመር ለማስጀመር ሁለት ትራንሰፎርመር እንደሚያስፈልግ አስታዉሰዉ በዞኑ መንግስት ድጎማ በመዉሰድ ወደ 2 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር ግዢ በማድረግ ችግሩን ለመቅረፍ ጥረት እየተደረገ እንደሆነም አስታዉቀዋል።

የወልቂጤ ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ዋና የመንግስት ተጠሪ አቶ ሙባሪክ አህመድ በበኩላቸዉ ከመድረኩ የተነሱ የማህበረሰቡ አስተያየቶች በአጭር ፣በመካከለኛና በረጅም ጊዜ አቅደን ለመፍታት ይደራል ብለዋል።

ህዝቡ የሚያነሳቸዉ የልማት ፣ የመልካም አስተዳድር እንዲሁም የአካባቢዉ ሰላም በማስጠቅ ረገድ ያሉ ችግሮች በዘላቂነት ለመቅረፍ ይሰራል ብለዋል።

ህገ ወጥ ነጋዴዎች ወደ መስመር እንዲገቡና ፍትሃዊ የግመታ ስራ በመስራት በገቢ አሰባሰብ ዘርፍ የተሻለ ስራ መስራት እንደሚገባም አስረድተዋል።

የከተማዉ የገቢ አቅም ለማሳደግ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታዩ ዉስንነቶች በመቅረፍ እንዲሁም የአካባቢዉ ሰላም በዘላቂነት በማስከበር ህዝቡ ከጸጥታ አካላቱ ጋር ተቀናጅቶ መስራት እንደሚገባም አብራርተዋል።

አንዳንድ የዉይይት ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ቀደም ሲል በከተማ አስፓልት ይሰራል ተብሎ የፈረሱት የዉስጥ ለዉስጥ የኮብል መንገዶች ያፈረሱ አካላት በህግ መጠየቅ እንዳለባቸዉም ጠይቀዋል።

ማህበረሰቡና ነጋዴዉ በሚከፍሉት ግብር በከተማዉ የሚጠበቀዉ ልማት ማምጣት እንዳልተቻለ አመላክተዉ በከተማዉ በልማትና በመልካም አስተዳድር ዙሪያ እየተሰራ ያለዉን ስራ ለህዝቡ በየሶስት ወሩ ሪፖርት ለህዝብ መቅረብ ይኖርበታል ብለዋል።

የከማዉ የጸጥታ ሁኔታ በዘላቂነት በመፍታት ባለሀብቱ በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዲሰማራ መሰራት አለበት።

በከተማዉ በኢንቨስትመንት ዘርፍ ቦታ ተሰጥቷቸዉ ወደ ልማት ያልገቡ ለአብነት ያህል ተፈራ ሆቴል የተሰጠዉ ሀይሌ ገብረስላሴና ሎሌዎችም ባለሀብቶች ወደ ልማቱ በአፋጣኝ መግባት እንዳለባቸዉም ተናግረዋል።

በከተማዉ የህግ የበላይነት በማረጋገጥ ሰላም በማስፈንና በልማት ዘርፍ ተጨባጭ ዉጤት ማምጣት እንደሚገባም አስረድተዋል።

ከነዋሪዉ የሚሰበሰበዉ ግብር ለታለመለት ዓላማ እየዋለ ስለመሆኑ በተገቢዉ ክትትል መደረግ እንዳለበት አሳስበዋል ሲል የዘገበዉ የጉራጌ ዞን መንግስት ኮሚኒኬሽን መምሪያ ነዉ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *