ለሰላም ቅድሚያ በመስጠትና በከተማዉ በመሰረተ ልማት ዝርጋታ ያሉ ችግሮች መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ሊቀርፍላቸዉ እንደሚገባ የአረቅጥ ከተማ ነዋሪዎች ጠየቁ።

የካ

ሁሉን አቀፍ የህዝብ ተሳትፎ ለብልጽግና ጉዟችን ስኬታማነት በሚል መሪ ቃል ከተማ አቀፍ ህዝባዉ የዉይይት በአረቅጥ ከተማ ተካሄዷል።

በማዕከላዊ ክልል ቴክኒክና ሙያ ቢሮ ሀላፊና የእለቱ የክብር እንግዳ አቶ ይርጋ ሀንዲሶ በህዝብ ዉይይት መድረኩ ተገኝተዉ እንዳሉት ወጥቶ መግባት የሚቻለዉ ሰላም ሲኖር እንደሆነም አመላክተዉ ህዝቡ ለአካባቢዉ ሰላም ልዩ ትኩረት ሊሰጠዉ ይገባል።

ለእኛ የሚጠቅመን መቻቻል ፣ መከባበርና የህዝቦች አንድነት በማጠናከረ አብሮነትን ማጎልበት እንደሚገባም አብራርተዋል።

በግል ጥቅማቸው የታወሩ ጥቂት ሃይሎች የማህበረሰቡን ሰላም ለማደፍረስ መሞከራቸው አይቀርም ያሉት ሃላፊው መሰል ሃይላትን በጋራ መመከት ይገባል ብለዋል።

የሰላም ጉዳይ እንደክልል ቅድሚያ ተሰጥቶ እየተሰራበት እንደለም በማከል።

የመብራትና ሌሎችም የከተማ ልማቶችን ጨምሮ በመድረኩ የተነሱ ጥያቄዎች ለሚመለከተው አካል በማድረስ ምላሽ እንዲሰጥበት ይደረጋልም ብለዋል።

ክልሉ አዲስ የተደራጀ እንደመሆኑ መጠን ብዙ የልማት ጥያቄዎች ያሉበት እንደሆነ ያነሱት አቶ ይርጋ ሃንዲሶ እነዚህን ጥያቃዎች ደረጃ በደረጃ ለመፍታት በየአካባቢው ያሉ እምቅ አቅሞችን በማስተባበር የሃብት መፍጠር ስራ መሰራት እንዳለበትም ተናግረዋል።

ህዝቡ በመድረኩ ያነሳቸዉን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ የሚፈታና ይህንንም ጥያቄ ለሚመለከተዉ አካል የሚያቀርቡም እንደሆነም ተናግረዋል።

የአረቅጥ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ መንግስቱ ሹሜ እንዳሉት አባቶቻችን የፈጸሙትን የጀግንነት ተግባር ለመጪ ትዉልድ ለማስተላለፍና የህዝቦች አንድነት ለማጠናከር ታስቦ የተዘጋጀ የዉይይት መድረክ ነዉ።

በመዲናችን አዲስ አበባ የተገነባዉ ትልቁ የአድዋ ሙዚየም በተመረቀበት ሳምንት የህዝብ ዉይይት መደረጉም ታሪካዊ የሚያደርገዉ ሲሆን ይህ ፕሮጀክት በአጭር ጊዜ ዉስጥ ተገንብቶ እንዲጠናቀቅ የለዉጡ መንግስታችን ያላቸዉን አክብሮት ገልጸዋል።

በለዉጡ መንግስት በሀገሪቱ የተጀመሩ ሁለንተናዊ ለዉጥና የብልጽግና ጉዞ ለማጠናከር እንዲሁም ተግዳሮቶችን በዉይይትና በንግግር ለመፍታት ሁሉን አቀፍ የህዝብ ተሳትፍ የብልጽግና ጉዞችን በየደረጃዉ የሚደረጉ ዉይይቶች ፋይዳቸዉ ከፍተኛ መሆኑም አመላክተዋል።

በዉይይት መድረኩ የተነሱ የልማት ጥያቄዎች ተገቢነት ያላቸዉና በቀጣይ ደረጃ በደረጃ መንግስት ከህዝቡ ጋር በመሆን በቅንጅት እንደሚፈታቸዉም አስታዉቀዋል።

የጉራጌ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ረዳት የመንግስት ተጠሪ ወይዘሮ አመተረዉፍ ሁሴን በበኩላቸዉ ህብረ ብሔራዊ ወንድማሟችነትና እህትማማችነት ለዘላቂ ሰላምና ለሁለንተናዉ ብልጽግና በሚል ዉይይት እየተደረገ እንደሆነም ተናግረዉ በዞኑ በ44 ከተማ መዘጋጃ ቤቶችና በ4 ከተማ አስተዳደር ጨምሮ ዉይይት እየተደረገ እንደሆነም አስታዉቀዋል።

የህዝብ ዉይይቶች በየአካባቢዉ ማህበረሰቡ በተጨባጭ የሚያነሳቸዉ ጥያቄዎች፣ ድክመቶችና ጠንካራ ጎኖች የሚነሱበትም እንደሆነም አመላክተዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የሚመራዉ መንግስታችን ትልቁ ነገር ለሰላም የሰጠዉ ዋጋ ከፍተኛ ሲሆን የትኛዉም አካል ጥያቄ ቢኖረዉ በጠረጴዛ ዙሪያ በመነጋገር መፍታት እንደሚገባም አስረድተዋል።

የህግ የበላይነት በማረጋገጥ የማህበረሰቡ ሰላም ማስጠበቅ ይገባል ያሉት ወይዘሮ አመተረዉፍ ሁሴን በመነጋገር ዘላቂ ሰላም በማስፈን ዉጤታማ ስራ እንደሚሰራም አብራርተዋል።

በመድረኩ ህዝቡ ያነሳቸዉን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ለመቅረፍ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

በከተማ ደረጃ በርካታ የልማት ስራዎች በቅንጅት እየተሰራ ሲሆን ያሉንን አቅም በመጠቀምና ባለሀብቶች በመሳብ ለወጣቱ የስራ ዕድል መፍጠር እንደሚገባም አስረድተዋል።

በመድረኩ የተገኙ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች እንዳሉት
በከተማዉ ህገወጥ ግንባታ ማስቆም ፣የንጹሁ መጠጥ ዉሃ ችግር ፣ ቀድመዉ የተጀመሩ ያልተጠናቀቁ የመንገድ ግንባታ በማጠናቀቅ ማህበረሰቡ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።

ማህበረሰቡ ፍትሃዊ የጤና አገልግሎት እንዲያገኝ የሆስፒታል ግንባታ ፣የመብራት መቆራረጥና የትራንስፎርመር ጥያቄዎች በስፋት የሚነሱም እንደሆነም ተናግረዉ የወጣቱ የስራ ዕድል ከመፍጠር ጋር ያሉ ዉስንነቶች በመቅረፍ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸዉን ማጎልበት እንደሚገባም ጠይቀዋል።

በትራንስፖርት ዘርፍ ከሆሳና አረቅጥ እና ከወልቂጤ አረቅጥ በአግባቡ ትራንስፖርት በቋሚነት ተሽከርካሪ ተመድቦ ሊሰራ ይገባል ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ ከወልቂጤ አረቅጥ ሲመጡ በሆሳና ታሪፍ እንደሚከፍሉና ህዝቡ ለተጨማሪ ክፍያ እየተዳረገ እንደሆነም አብራርተዋል።

ለሰላም ቅድሚያ በመስጠትና በከተማዉ በመሰረተ ልማት ዝርጋታ ያሉ ችግሮች መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ሊቀርፍላቸዉ እንደሚገባም ጠይቀዋል።

በህዝባዊ ዉይይት መድረኩም የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቴክኒክና ሙያ ቢሮ ሀላፊ አቶ ይርጋ ሀንዲሶ፣ የዞኑ ብልጽግና ፓርቲ ረዳት የመንግስት ተጠሪ ወይዘሮ አመተረዉፍ ሁሴን ፣ የጉራጌ ዞን ባህል ቱሪዝም መምሪያ ሀላፊ ወይዘሮ መሰረት አመርጋ አንዲሁም የአረቅጥ ከተማና የጉመር ወረዳ ከፍተኛ የመንግስት ሀላፊዎች ፣ የሀይማኖት አባቶች ፣የሀገር ሽማግሌዎች፣ ከየማህበራዊ ዘርፎች የተዉጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊዎች ነበሩ ሲል የዘገበዉ የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን መምሪያ ነዉ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *