ለማህበራዊ ችግር ተጋላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የተለያዩ ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል በትኩረት እንደሚሰራ የጉራጌ ዞን ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ገለጸ።

መምሪያው የ2015 በጀት አመት የ11 ወር የተግባር አፈጻጸም ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በወልቂጤ ከተማ ገምግሟል።

የጉራጌ ዞን ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ አቶ መኩሪያ ተመስገን በወቅቱ እንደገለጹት ከመንግስት በጀት በተጨማሪ ከባለሀብቶች፣ ከተለያዩ ድርጅቶች፣ ከማህበረሰብና ከሌሎችም ሀብቶችን በማሰባሰብ ለማህበራዊ ችግር ተጋላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የተለያዩ ድጋፎች ተደራሽ መደረጉን ገልጸዋል።

ከዚህም ባለፈ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከልና ህጋዊ የስራ ስምሪት በውጭ ሀገር ለማጠናከርና ሌሎችም በርካታ አመረቂ ተግባራት ተሰርቷል ብለዋል።

በቀጣይ ከዚህ በፊት የነበሩ ክፍተቶችን በማረም ለማህበራዊ ችግር ተጋላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ እንደሚሰራ ተናግረዋል ።

የግምገማ መድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት በተግባር አፈጻጸም ወቅት የነበሩ ክፍቶችን በማረም በቀጣይ የተሻለ ስራ ለመስራት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ተግባራቶችን በተፈለገው ልክ ለመፈጸም የሰው ሀይል፣ የበጀትና የተሽከርካሪ እጥረት መኖሩን ገልጸው ይህንም ለመቅረፍ የሚመለከታቸው አካላት በትኩረት መስራት እንዳለባቸው አመላክተዋል ።

በእለቱም የሙያ ደህንነት ጤንነት ኮሚቴ አወቃቀር ፣የውጭ ሀገር የሰራ ስምሪት እና የቤተሰብ ተቋም ግንባት ስልጠና ተሰጥቷል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *