ለህብረተሰቡ የሚሰጡ የጤና አገልግሎቶች በፍትሃዊነት ተደራሽ ለማድረግና ጥራታቸውን የጠበቁ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የጉራጌ ዞን ጤና መምሪያ አስታወቀ፡፡

በዞኑ ጤና መምሪያ ባለፉት 6 ወራት የተከናወኑ ተግባራት እቅድ አፈጻጸም ላይ ትኩረት ያደረገ የውይይት መድረክ በወልቂጤ ከተማ ተካሂዷል፡፡

የጉራጌ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ አየለ ፈቀደ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት ባለፉት 6 ወራት ለህብረተሰቡ የሚሰጡ የጤና አገልግሎቶች ፍትሃዊ፣ ተደራሽና ጥራታቸውን የጠበቁ ለማድረግ በርካታ ጥረቶች ተደርጓል፡፡

በዚህም ከ80 ከመቶ የሚሆኑ እናቶች የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት መጠቀማቸው፣ 92 ከመቶ የሚሆኑ ህጻናት ክትባት ማግኘታቸው፣ እናቶች የቅድመ ወሊድ ምርመራ እየተደረገላቸው የመውለጃ ጊዜያቸው ሲደርስ በጤና ተቋማት በተዘጋጀላቸው ማረፊያ ቤት ሆነው በሰለጠኑ ባለመያዎች እገዛ እንዲወልዱ የተሻለ አፈጻጸም የታየባቸው ተግባራት መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

በዞኑ ተከስቶ የነበረው የወባ ወረርሽኝ ለመቆጣጠር በተሰራው ስራ በሰው ህይወት ላይ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ ስርጭቱን በአጭር ጊዜ መቆጣጠር መቻሉ እንዲሁም ማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ተግባራዊ በማድረግ አነስተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች በህመማቸው ልክ እንዲታከሙ የማስቻል ስራ በተሻለ ደረጃ መፈጸማቸውን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

በቀጣይ የቲቢ በሽታ ልየታ፣ በሆስፒታሎች ሞተው የሚወለዱ ህጻናት ቁጥር መቀነስ፣ ክትባት ጀምረው የሚያቋርጡ ህጻናት እንዳይኖር ማድረግ እንዲሁም ወረርሽን ቢከሰት በአጭር ጊዜ በመከላከል የመቆጣጠር አቅም ማሳደግ ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራ አቶ አየለ ገልጸዋል፡፡

የጤና አክስቴንሽ አዲሱ ፍኖተ ካርታ ተግባራዊ በማድረግ ህብረተሰቡ የተሻለ የጤና አገልግሎት እንዲያገኝ ለማስቻል በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል የጌታ ወረዳ የጤና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሳዲቅ ጀማል በ6 ወራት የእቅድ አፈጻጸም ላይ በሰጡት አስተያየት እናቶች በወሊድ ምክንያት እንዳይሞቱ የሚደረገው የጤና ክትትልና እንከብካቤ፣ ህብረተሰቡ የግሉንና የአካባቢውን ንጽህና በመጠበቅ ሞዴል ቀበሌዋች ለመፍጠር እየተሰራ ያለው ስራ አበረታች መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የእንድብር ከተማ አስተዳደር ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጣሰው ታደሰ በውይይቱ በቀጣይ እንዲስተካከሉ የሚሉዋቸው ነጥቦች ላይ አስተያየት እንዲሰጡን ጠይቀናቸው እደተናገሩት የጤና ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ የመድሃኒት አቅርቦት ችግር መቅረፍ፣ የጤና አክስቴሽን አገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻል፣ ምቹ የስራ አካባቢ በመፍጠር የባለሙያ ፍልሰት መከላከል ላይ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው ሊሰሩ ይገባል ማለታቸው የዘገበው የጉራጌ ዞን መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *