ህጻናት በዕዉቀትና በስነ -ምግባር እንዲታነጹ በማድረግ የሀገራቸውን ባህል በጠበቀ መልኩ እንዲያድጉ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ሀላፊነት እንዳለበትም የጉራጌ ዞን ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ መምሪያ አስታውቀ፡፡

የዞኑ የህጻናት ፓርላማ 8ኛ ዓመት 15ኛ ዙር 1ኛ መደበኛ ጉባኤ በወልቂጤ ከተማ ከሁሉም ወረዳዎችና ከተማ አስተዳድሮች የተዉጣጡ የህጻናት ፓርላማ ተወካዮች እንዲሁም የጉራጌ ዞን ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ መሰረት አመርጋ፣የዞኑ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ክብርት ወ/ሮ አርሺያ አህመድ እንዲሁም የፓርላማው ቋሚ ኮሚቴዎችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተሳታፊዎች በተገኙበት ተካሄዷል።

በጉባኤው ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የጉራጌ ዞን ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ መሰረት አመርጋ እንደገለጹት የዞኑ የህጻናት ፓርላማ ከተመሰረተ ስምንት አመት ያስቆጠረ ሲሆን በዚህ ሂደት ውስጥ በሚሰሯቸው መልካም ተግባራትና እየሰሯቸው ያሉ መልካም ተሞክሮዎች እንደ ዞን ብቻ ሳይሆን እንደ ክልል እንዲሁም እንደ ሀገር በምርጥ ተሞክሮነት በርካቶች መጥተው ዕውቀትና ተሞክሮ የቀሰሙበት እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

ህገ ወጥ የህጻናት ዝውውር፣የህጻናት የመብት ጥሰትና የተለያዩ ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶቻቸው እንዲጠበቁ የዞኑ የህጻናት ፓርላማ የማይተካ ሚና እንደተጫወተ እንደሆነም አስታዉቀዋል።

በዚህም በዞን ደረጃ ብቻ በ 2013 እና 2014 አመተ ምህረት በአመት እስከ 2 መቶ ሺ ብር በመበጀት እንዲሁም ታች ባሉ መዋቅሮችም ከመንግስት በጀት ተቀናሽ በማድረግ ፓርላማው አባላት እንዲጠናከሩ ትልቅ ስራ መሰራቱም አብራርተዋል።

የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ክብርት ወ/ሮ አርሺያ አህመድ በበኩላቸዉ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በጦርነት ምክንያት ህጻናትና ሴቶች ላይ እየተደረገ ያለውን ኢ- ሰባአዊ ድርጊት አውግዘው ይህንንም ድርጊት እንዳይደገም ከሚመለከታቸው አካላት በጋራ በመሆን በቅንጅት መሰራት እንዳለበትም አስረድተዋል።

አክለዉም የህጻናት ፓርላማ የተወከሉ አባላት በህጻናት ላይ የሚደርሰውን ጥቃትና ህገወጥ ዝዉዉርን በመከላከል ረገድ የበኩላቸዉን መወጣት እንዳለባቸዉም አሳስበዋል።

የጉራጌ ዞን የህጻናት ፓርላማ ፕሬዝዳንት ክብርት ራሂማ ዩሀንስ እንደገለጹት በባለፉት ጊዜያት በህጻናት መብትና አላስፈላጊ ድርጊቶች ለማስቆም ብዙ ስራዎች መሰራቱንና በቀጣይም አዲስ ከሚሾሙት የፓርላማው አባላት ጋር በጋራ በመሆን በሀላፊነት እንደሚሰሩም አስረድተዋል።

በጉባኤው የተገኙ አንዳንድ ተሳታፊዎችበሰጡት አስተያየት ህጻናት ከገጠር ወደ ከተማ እየተሰደዱ ላላስፈላጊ ድርጊትና የጉልበት ብዝበዛ እየተዳረጉ እንደሆነና ይህንንም ድርጊት ለማስቆም ከህጻናት ፓርላማው በተጨማሪ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ርብርብ ማድረግ እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

በጉባኤው ጊዜያቸውን የጨረሱ የፓርላማው ስራ አስፈጻሚዎች በአዲስ የመተካት ስራ ተከናውኗል፡፡

በዚህም መሰረት ስራ አስፈጻሚዎች የነበሩ ራሂማ ዩሀንስ ፣ ሊዲያ ሞገስ ፣ጽናትሞገስ በአዲስ የተተኩት ሲሳይ ጥላሁን ዋና አፈ ጉባኤ፣ቶፊቅ ጁነይድ ምክትል አፈ ጉባኤና አዲስ ተመስገን ጸሀፊ ሆነዉ ተሹመዋል።

ከዚህም በተጨማሪም ቋሚ ኮሚቴዎች በፊት የነበሩ ዚያድ ጀማል፣ወቂያስ ሆነልኝ፣አዳነ ዱላ፣ሀናን ሙህዲን፣ገነት ፍቃዱ ሰውዳ ቶፊቅ በአዲስ ኮሚቴዎች ፍልሰታ ዱላ፣ እየሩሳሌም አሰፋ፣ዮሐንስ አየለ፣ለማ ከማል፣ሄኖክ ተመስገን፣ረጂብ ሙራድ የጉባኤው አባላት በሙሉ ድምጽ ጸድቆላቸዋል፡፡

የሁሉም ወረዳዎችና ከተማ አስተዳድሮች የህጻናት ፓርላማ ተወካዮች፣የጉራጌ ዞን ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ መሰረት አመርጋ፣የዞኑ ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ ክብርት ወ/ሮ አረሺያ አህመድ እንዲሁም የፓርላማው ቋሚ ኮሚቴዎችና ሌሎችም ባለ ድርሻ አካላት የተሳተፉ ሲሆን በእለቱም ለተሰናባቾቹ የፓርላማዉ አባላት የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው

  • አካባቢህን ጠብቅ!
  • ወደ ግንባር ዝመት!
  • መከላከያን ደግፍ!
    በተጨማሪም እነዚህ ሊንኮችን በመጫን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡
    Facebook:- https://www.facebook.com/gurage1Zone
    Website:- https://gurage.gov.et
    Telegram:- https://t.me/comminuca
    Youtub: -https://www.youtube.com/channel/UCzrcazGvvIO2tG7bQN36Cx

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *