ህጻናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መማራቸው የትምህርት ጥራት ከማረጋገጥ ባለፈ ቋንቋው ይበልጥ እንዲያድግ ሚናው ከፍተኛ በመሆኑ በዘርፉ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባ የጉመር ወረዳ ትምህርት ጽህፈት ቤት ገለጸ።


የጉራጊኛ ቋንቋ ትምህርት በዞኑ በ8መቶ 60 ቅድመ መደበኛና አጸደ ህጻናት እና በ403 በመንግስትና በግል አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በመደበኛነት ከመስጠት ባለፈ በ18 ትምህርት ቤቶች የ2ኛ ክፍል የሙከራ ትምህርት እየተሰጠ ይገኛል።

የጉመር ወረዳ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዲሱ ሰማኔ በወረዳው በ25 ትምህርት ቤቶች በቅድመ መደበኛና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እየተሰጠ መሆኑ ጠቅሰው በ2ኛ ክፍል ትምህርት ቤቶች የሙከራ ትምህርት መጀመሩን አንስተዋል።

ተማሪዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መማራቸው የትምህርት ፍላጎታቸው ከማሳደጉም ባለፈ ቋንቋ እንዲያድግ ሚናው ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው ለዚህም የዞኑ መንግስት ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በወረዳው 107 መምህራን በመመደብ የመማር ማስተማሩ ስራ በጥሩ ሁኔታ እየተሰጠ መሆኑን ገልጸው የመምህራን አቅም ለማሳደግ ስልጠና ለመስጠት ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል።

የቅድመ መደበኛና አንደኛ ክፍል የጉራጊኛ የመማሪያና ማስተማሪያ መጽሀፍ ለማሟላት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸው የ2ተኛ ክፍል የመጽሀፍ እጥረት ለመቅረፍ እንደሚሰራም ነው ያነሱት።

የጉራጊኛ ቋንቋ ለማሳደግ ህብረተሰቡና መንግስት በመቀናጀት እየሰሩት ያለው ስራ የተሻለ መሆኑን ገልጸው በቀጣይም ይበልጥ ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በጉመር ወረዳ የቦሌ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የጉራጊኛ ትምህርት መምህርት ወይዘሮ ገነት ተሬ በበኩላቸው ህጻናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው በመማራቸው ህጻናቱም ይሁን ህብረተሰቡ ደስተኛ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ህጻናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መማራቸው የትምህርት ጥራት እንዲረጋገጥና ቋንቋው እንዲጎለብት ሚናው ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው ይህም መንግስት በጀመረው ልክ አጠናክሮ ሊያስቀጥለው ይገባል ብለዋል።

የዞኑ መንግስት ቋንቋው ለማሳደግ የጀመረው ስራ አድንቀው ቋንቋው ይበልጥ እንዲያድግና እንዲጎለብት አስፈላጊውን ድጋፍና እገዛ ማድረግ እንዳለበት ተናግረዋል።

የ2ተኛ ክፍል የመማሪያና ማስተማሪያ መጽሐፍ እጥረት እንዳለ ያነሱት መምህሯ ለዚህም የሚመለከተው አካል ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም አመላክተዋል።

ከዚህም ባሻገር መንግስት የመምህራን እጥረትና አቅማቸውን ለማሳደግ ብሎም የግብአት ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት መስራት እንዳለበት ተናግረዋል።

ህጻን ሀዲ ከድር ከ1ኛ ክፍል፣ ህጻን ሀጀራ ማህሙድና ከኬጂ ክፍልና አብድልካፍ አብድራሂም ከ1ኛ ክፍል በጉራጊኛ የጉራጊኛ ፊደላት፣ ቁጥር፣ ወራቶች፣ መዝሙራትና ሌሎችም እየተማሩ ይገኛሉ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *