ህጻናት በተወለዱ 1ሺህ ቀናት የምንመግባቸው የተመጣጠነ ምግብ ጤናው የተስተካከለና አምራች ዜጋ ለመፍጠር ሚናው የጎላ በመሆኑ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ሊረባረብ እንደሚገባ የጉራጌ ዞን ጤና መምሪያ አስታወቀ፡፡

ሰኔ 23/2015 ዓ.ም

ህጻናት በተወለዱ 1ሺህ ቀናት የምንመግባቸው የተመጣጠነ ምግብ ጤናው የተስተካከለና አምራች ዜጋ ለመፍጠር ሚናው የጎላ በመሆኑ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ሊረባረብ እንደሚገባ የጉራጌ ዞን ጤና መምሪያ አስታወቀ፡፡

ዘራይት ቱ ግሮው ከጉልባማ ጋር በመተባበር በዞኑ ስርዓተ ምግብ ለማሻሻል እያከናወኑት ያሉትን ተግባራት ላይ ትኩረት ያደረገ ውይይት ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በወልቂጤ ከተማ ተካሂዷል፡፡

የጉራጌ ዞን ዋና የመንግስት ተጠሪ አቶ መሰለ ጫካ በውይይቱ ላይ እንደገለጹት አመራሩና ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው የልማት ስራዎች በመስራት ህብረተሰቡ በቀን 3 ጊዜ መመገብ እንዲችል መረባረብ ይኖርባቸዋል፡፡

የተሻለ ሀገር ሊገነባ የሚችል ትውልድ ለመፍጠር የህብረተሰቡ የስርዓተ ምግብ ሁኔታ ሊሻሻል እንደሚገባ የገለጹት አቶ መሰለ ጫካ ይህንን ተግባር ውጤታማ ለማድረግ የፕሮጀክቱ ተጠቃሚ የሆኑ ወረዳዎች ተገቢውን የበጀት ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

የጉራጌ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ሰለሞን ጉግሳ በውይይቱ ላይ እንዳሉት በሀገሪቱ የስርዓተ ምግብ ችግር ስር የሰደደ በመሆኑ ይህንን ሁኔታ ለመቀየር ከፌደራል መንግስት ጀምሮ በተለየ ትኩረት በመስጠት በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡

ህጻናት በተወለዱ 1ሺህ ቀናት የምንመግባቸው የተመጣጠነ ምግብ ጤናው የተስተካከለና አምራች ዜጋ ለመፍጠር ሚናው የጎላ በመሆኑ ይህንን ተግባር በዞኑ ውጤታማ ለማድረግ የሚመለከታቸው ሴክተር መስሪያ ቤቶች ከባለድርሻ አከላት ጋር ተቀናጅተው ሊሰሩ እንደሚገባ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

ዘራይት ቱ ግሮው ከጉልባማ ጋር በመተባበር በዞኑ በ6 ወረዳዎች ላይ ስርዓተ ምግብ ለማሻሻል እየሰሩ መሆናቸውን የገለጹት አቶ ሰለሞን ጉግሳ ተግባሩ ውጤታማ ለማድረግ በቴክኒክና በአቢይ ኮሚቴ ከሚመራበት ወደ ስርዓተ ምግብ ምክር ቤት በማሳደግ ይሰራል ብለዋል፡፡

አክለውም በቀጣይ የፕሮጀክቱ ተጠቀሚ በሆኑ ስድስት ወረዳዎች ላይ ለተሞክሮ የሚሆኑ ተግባራት በመፈጸም በዞኑ የሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች እንዲሰፋ ለማድረግ ከመቼውም ግዜ በላይ ባለድርሻ አካላት ህብረተሰቡን በይበልጥ ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችል የጋራ እቅድ በማቀድ መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

ዘራት ቱ ግሮው ፕሮጀክት አስተባባሪ ወ/ሮ ምስራቅ አድማሱ በበኩላቸው ድርጅታቸው ከጉልባማ ጋር በመተባበር የስርዓተ ምግብ ችግር ለመቅረፍ መንግስት ያወጣቸውን ፖሊሲዎች ተፈጻሚ እንዲሆኑ የመደገፍ ስራ እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ይህንንም እውን ለማድረግ ህብረተሰቡ የራሱ ችግር እራሱ እንዲፈታ ግንዛቤ በመፍጠር የማነሳሳት ስራ እየሰሩ መሆናቸውን የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ገልጸዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ዘራይት ቱ ግሮው ከጉልባማ ጋር በመተባበር ስራ ከጀመረ 2 ዓመት ወዲህ የህብረተሰቡ ስርዓተ ምግብ ለማሻሻል እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት የሚበረታቱ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በዞኑ የሚገኘው የአየር ንብረት ሁሉንም አይነት ሰብሎች፣ አትክልትና ፍራፍሬ ለማልማት ተስማሚ በመሆኑ ህብረተሰቡ በጓሮው እያመረተ የአመጋገብ ስርዓቱ ለማሻሻል የሚመለከታቸው ሴክተር መስሪያ ቤቶች ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅተው እንዲሰሩ እንደሚያደርጉ ተናግረው የዞን ተቋማትም በተዋረድ የሚገኙ መዋቅራቸውን የስርዓተ ምግብ ጉዳይ እንደ አንድ ተግባር በዕቅድ አካተው እንዲፈጽሙ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

በመጨረሻም የጋራ እቅድ ስምምነት ተፈራርመዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *