ህገወጥ የንግድ ስርዓት በመቆጣጠር የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸው የጉራጌ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ አስገነዘበ።

መምሪያው በ2014 በጀት እመት በመጀመሪያ ግማሽ አመት የተሰሩ ስራዎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በወልቂጤ ከተማ መገምገሙን ተመልክቷል ።

የዋጋ ንረት በተፈጥሮ ወይም በሰው ሰራሽ ምክንያት የሚፈጠር የአቅርቦት እጥረት ሲሆን የዜጎችን ህይወት በእጅጉ ይጎዳል።

በተፈጥሮ ምክንያት የሚከሰት የአቅርቦት እጥረት በህግ መከላከል የማይቻል ክስተት ሲሆን ሰው ሰራሽ የአቅርቦት እጥረት ደግሞ ህግን በማስከበር እጥረት እንዳይከሰት ማድረግ ይቻላል።

ለዚህ ደግሞ በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካላት ህገወጥ የንግድ እንቅስቃሴ ለማስቆም ተቀናጅተው መስራት ሲችሉ መሆኑን የመምሪያው ኃላፊ አቶ መሀመድ አማን ገልጸዋል።

እንደ ኃላፊው ገለፃ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከተ የመጣው ህገወጥ የቤንዚንና ናፍጣ ሽያጭ፣ ያለደረሰኝ የሚደረግ ሽያጭ ፣ የመንገድ ዳር ንግድ፣ የመሰረታዊ ፍጆታ እቃዎች አቅርቦት እጥረት የዜጎች ኑሮ ፈታኝ አድርገውታል።

እነዚህ ችግሮች በዘላቂነት በመቅረፍ ዜጎች ተጠቃሚ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚገባ አቶ መሀመድ ገልፀዋል።

እስካሁን በከተሞችና በወረዳ አስተዳደሮች በቤንዚን ሽያጭ ፍቃድ የተሰጣቸው ነጋዴዎች እንደሌሉ የገለጹት ሃላፊው በቀጣይ በእነዚህ ህገወጥ ነጋዴዎች ህጋዊ እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል።

እንደ ኃላፊው ገለፃ የአቅርቦት እጥረት እንዲከሰት በማድረግ የዋጋ ንረትን በሚያባብሱ ነጋዴዎችና ድርጅቶች ህጋዊ እርምጃ የሚወሰድ ሲሆን በየደረጃው የሚገኙ የመዋቅሩ አመራሮችና ባለሙያዎች በቁርጠኝነት መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

ሸማቹ ማህበረሰብ መግዛት የሚፈልገውን የግብርና እና የኢንዱስትሪ ውጤቶች በተመጣጣኝ ዋጋ የሚያገኝበት ሳምንታዊ ቅዳሜ ገበያን በዞኑ ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን የተጠቃሚዎች ፍላጎት ሊያሟሉ የሚችሉ ምርቶች እንዲቀርቡ ይደረጋል ብለዋል።

አንዳንድ ወረዳዎች የግብርና ውጤቶች ከዩኒየንና ከሌሎች አምራች ወረዳዎች ጋር ትስስር በመፍጠር ምርትን ለህብረተሰቡ በማቅረብ የህብረተሰቡን የኑሮ ጫና ለመቀነስ እየሰሩ ሲሆን ሌሎችም የወረዳና ከተማ አስተዳደሮች ልምድ በመቅሰም ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ መስራት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በገበያ ላይ የሚስተዋለው የዋጋ ግሽበት ለማረጋጋት ምርትን በገፍ ወደ ገበያ ማቅረብ ይገባል ብለዋል ።

በወረዳዎች መካከል የሚደረግ የገበያ ትስስር ህብረተሰቡ በኑሮ ውድነት ምክንያት የሚደርስበትን ጫና የሚቀንስለት በመሆኑ በአንድ ወረዳ የሚመረት ጥራት ያለው ምርት ለሌላ ወረዳ ለማቅረብ የዘርፉ ባለሞያዎች በትኩረት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

አክለውም ተሳታፊዎቹ ዩኒየኖች እና ሸማች ማህበራት የግብርና እና የኢንዱስትሪ ውጤቶች ለሸማቹ ማህበረሰብ በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ኃላፊነታቸው እንዲወጡ አሳስበዋል።

ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች ከመምሪያው የማኔጅመንት አባላት ምላሽ በመስጠት ጉባኤው ተጠናቋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

በመረጃ ምንጭነት ገጻችን ምርጫዎ ስላደረጉ እናመሰግናለን!!
= ኢትዮጵያን እናልማ!
= የፈረሰውን እንገንባ!
= ለፈተና እንዘጋጅ!
በተጨማሪም እነዚህ ሊንኮችን በመጫን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡
Facebook:-
https://www.facebook.com/gurage1Zone
Website:- https://gurage.gov.et
Telegram:- https://t.me/comminuca
Youtub: -https://www.youtube.com/channel/UCzrcazGvvIO2tG7bQN36Cx!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *