የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ በችግኝ ተከላው ወቅት ተገኝተው እንዳሉት በዞኑ በዘንድሮ አመት ከ70 ሚሊዮን በላይ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን የሚተከል ሲሆን ከነዚህም 2ነጥብ 5 ሚሊዮን የፍራፍሬ፣ 14 ሚሊዮን የቡናና ከ20 ሚሊዮን በላይ የመኖ ችግኝ እየተተከለ ይገኛል።
ከዚህ ቀደም በመናኸሪያው የነበሩ ህገወጥ አሰራሮችን በመቅረፍ መናኸሪያውን የማዘመንና ለተገልጋዮች ምቹ አካባቢ ለመፍጠር እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በዛሬው እለት በወልቂጤ ከተማ መናኸሪያ ለምግብነትና ለጥላ የሚሆኑ ችግኞችን መተከሉን ያነሱት አቶ አበራ እነዚህ ችግኞች ለመናኸሪያው ውበት ከመሆናቸው ባለፈ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዳላቸውም ገልጸዋል።
በዞኑ በሁሉም የመንግስትና የግል ተቋማት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን በመትከል ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
መናኸሪያው ለተገልጋዮች ውብ፣ ሳቢና ማራኪ እንዲሆን ለማድረግ ችግኝ በመትከል እየተሰራ ያለው ስራ በማጠናከር የተተከሉ ችግኞችም የጽድቀት መጠናቸው ከፍ እንዲል ሁሉም የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
የጉራጌ ዞን ትራንስፖርትና መንገድ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙራድ ከድር በበኩላቸው እንደ ሀገር የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር መምሪያው እቅድ በማቀድ በዞኑ በሚገኙ ሁሉም መናኸሪያዎች ለምግብነትና ለጥላ የሚያገለግሉ ችግኞች ለመትከል እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
የወልቂጤ ከተማ መናኸሪያ ግንባር ቀደምና በርካታ እንግዶች የምታስተናግድ መሆኑን ተከትሎ ለተገልጋይ ማህበረሰብ ምቹ ለማድረግ ከ2 አመት ወዲህ በመናኸሪያው የነበሩ ህገወጥነት የማስተካከልና አረንጓዴ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዚህም በርካታ ህገወጥ ደላሎች የማስወገድ፣ በችግኝ የማስዋብ ስራዎች እየተሰራ ነው ያሉት ኃላፊው በዛሬው እለትም ህገወጥነትን በመንቀል ህጋዊ አሰራሮችና ችግኝ መትከል በሚል መናኸሪያው ውብና ሳቢ ለማድረግ ለጥላና ለምግብነት የሚውሉ ችግኞችን መተከሉንም አመላክተዋል።
የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ትግስቱ ተኸልቁ በባለፉት አመታት በመናኸሪያው የነበሩ ችግሮችን ለማስተካከል በተለይም የመግቢያና መውጫ በር የማሰራት፣ ለተገልጋዩ ማህበረሰብ መስመሮችን የሚጠቁሙ ታፔላዎች የመትከል፣ የጽ/ቤቱ ቢሮ የመጠገንና በግብአት የማሟላትና ግቢው ለተገልጋዩ ማህበረሰብ ውብ፣ ሳቢና ምቹ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
ተገልጋዩ ማህበረሰብ እንዳይንገላታና ትርፍ ክፍያ እንዳይከፍል 19 መስመሮች የኢ-ትኪቲንግ አገልግሎት እንዲሰጥ መደረጉን ነው ያነሱት።
ከዚህ ቀደም በመናኸሪያው የነበሩ ደላሎችና ህገወጥነት በማስተካከል ለተገልጋዩ ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉንም ኃላፊው ተናግረዋል።
በመናኸሪያው የተተከለው ችግኝ ለሶስተኛ ዙር መሆኑን የገለጹት አቶ ትግስቱ መናኸሪያው ውብና ሳቢ ለማድረግ በሚሰራው ስራ በዙሪያው ያሉ የማህበረሰብ ክፍሎች የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት እንዳለባቸው አንስተዋል።
በችግኝ ተከላው የተሳተፉ አካላት እንዳሉት መናኸሪያው ለተገልጋዮች ውብና ሳቢ ለማድረግ እየተሰራ ያለው ስራ አድንቀዋል።
በመናኸሪያው የተተከሉ ችግኞች እንዲጸድቁ የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ ገልጸው በመናኸሪያው የተጀማመሩ ስራዎች ይበልጥ አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።
በችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ የጉራጌ ዞን ረዳት የመንግስት ተጠሪ ወይዘሮ አመተሩፍ ሁሴን፣ የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ እንዳለ ስጦታው ጨምሮ የዞንና የከተማ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።