ህዳር 26/2014 የአመጋገብ ስርዓት በማሻሻል ጤናማ አምራችና ሀገር ተረካቢ ትውልድ ለማፍራት ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው ሊሰሩ እንደሚገባ የጉራጌ ዞን አስተዳደር አሳሰበ።

ሀንገር ፕሮጀክት በስርዓተ ምግብ አተገባበር ላይ ለተለያዩ ባለድርሻ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ዎርክ ሾፕ አዘጋጀ።

የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ የስርዓተ ምግብ ተግባር የአንድ ተቋም ተግባር ብቻ ባለመሆኑ ባለድርሻ አካላት በመቀናጀት ተግባሩ ውጤታማ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አስረድተዋል።

የስርዓተ ምግብ መጓደል በዜጎች ላይ የሚፈጥረው ተጽዕኖ ከፍተኛ መሆኑን የተናገሩት አቶ አበራ ሀገሪቱ ያላትን ሀብት የመጠቀምና በአለም ላይ ያላትን ተሰሚነት እንዲቀንስ ምክንያት ይሆናል ብለዋል። በመሆኑም የህጻናት የአመጋገብ ስርዓት በማሻሻል ጤናማ አምራችና ሀገር ተረካቢ ትውልድ ለማፍራት ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው ሊሰሩ እንደሚገባ አሳሰቡ።

የዞኑ ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ሸምሱ አማን በዞኑ በተለያዩ ወረዳዎች የሚገኙ የሴፍትኔት፣ የሀንገር ፕሮጀክት፣ ሴቭ ዘ ችልድረንና ኮንሰርን ኢትዮጵያ የተሰኙ ግብረሰናይ ድርጅቶች በስርዓተ ምግብ ፕሮግራም በመሰማራት ውጤታማ ተግባራት እያከናወኑ እንደሚገኙ አስረድተዋል።

በመሆኑም የህጻናት የመቀንጨር ችግር በመከላከል ብቁ፣ ተወዳዳሪና በራሱ የሚተማመን ሀገር ተረካቢ ትውልድ ለመፍጠር ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በሀንገር ፕሮጀክት ዘ ራይት ቱ ግሮው ፕሮጀክት ማናጀር ወይዘሮ ምስራቅ አድማሱ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ የሚተገበረው በሀገሪቱ በሶስት ክልሎች ማለትም በአማራ፣ በደቡብና በኦሮሚያ ክልሎች በሚገኙ 21 ወረዳዎች ከወርልድ ቪዥን፣ ከሀንገር ፕሮጀክት፣ ከማክስ ፋውንዴሽንና ከሲጋ እንዲሁም ከጉራጌ ልማትና ባህል ማህበር፣ ከኦርዳና ከሜስሚዶ ጋር በመተባበር እንደሆነ ገልጸዋል።

ዘ ራይት ቱ ግሮው ፕሮጀክት በኔዘርላንድ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሚያገኘው የገንዘብ ድጋፍ በጉራጌ ዞን በስድስት ወረዳዎች እድሜያቸው ከአምስት አመት በታች ለሆኑ ህጻናት በአመጋገብ ስርዓት፣ በውኃ አቅርቦት፣ በጤና አጠባበቅና በንጽህና አያያዝ ላይ የሚሰራ ፕሮጀክት ነው ብለዋል።

ዎርክሾፑ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በተለይም የዞንና የወረዳ አስተዳዳሪዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እንዲሁም አጋር ድርጅቶች በስርዓተ ምግብ አተገባበር ላይ የሚኖራቸው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ መፍጠር እንዲችሉ ያስችላቸዋል ብለዋል።

በመሆኑም ተሳታፊዎቹ ለህብረተሰቡ በስርዓተ ምግብ፣ በውሃ አቅርቦት፣ በጤና አጠባበቅና በንጽህና አያያዝ ላይ በንቃት እንዲሳተፍ ማንቃት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
የጉራጌ ልማትና ባህል ማህበር ዋና ዳይሬክተር አቶ ቅባቱ ተሰማ ማህበሩ በዞኑ እድሜያቸው ከአምስት አመት በታች የሆኑ ህጻናት በስርዓተ ምግብ ምክንያት የሚከሰቱ ችግሮች ለመከላከል ከሀንገር ፕሮጀክት ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

ፕሮጀክቱ በአበሽጌ፣ በቸሃ፣ በጌታ፣ በእንደጋኝ፣ በምሁርና አክሊል እና በገደባኖ ጉታዘር ወለኔ ወረዳዎች የሚገኙ ህጻናትን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

የስርዓተ ምግብ ተግባር ስኬታማ ለማድረግ በስድስቱ ወረዳዎች ቢሮ ከማመቻቸት በተጨማሪ ቢሮዎቹ በሰው ኃይልና በቁሳቁስ ማሟላት እንደተቻለም አቶ ቅባቱ ተናግረዋል።

በቀጣይ ማህበረሰቡ ያለውን ሀብት በአግባቡ እንዲጠቀም ለማንቃት ማህበሩ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
የዎርክ ሾፑ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት በምግብ ራስን ለመቻል ከሚደረገው እንቅስቃሴ ጎን ለጎን የአመጋገብ ስርዓት በማሻሻል ጤናው የተጠበቀ ንቁ ዜጋ ለመፍጠር የድርሻቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ ተናግረዋል።

በመሆኑም ዎርክሾፑ በየደረጃው የሚገኙ የስርዓተ ምግብ አብይና ቴክኒክ ኮሚቴዎች የተጣለባቸው ኃላፊነት በብቃት እንዲወጡ ያስችላል ብለዋል።

እንደ ተሳታፊዎቹ ገለጻ የውሃ፣ የግብርና፣ የጤናና ሌሎች ተቋማት የሚሰጡት አገልግሎት ለማሻሻል በቅንጅት መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

ስርዓተ ምግብ በአግባቡ በመተግበር በምግብ እጥረት ምክንያት የሚከሰቱ የህጻናት መቀንጨር፣ ከልክ በላይ መወፈር፣ አነስተኛ ክብደትና ሌሎች ተዛማጅ ችግሮች ለመቅረፍ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

  • አካባቢህን ጠብቅ!
  • ወደ ግንባር ዝመት!
  • መከላከያን ደግፍ!

በተጨማሪም እነዚህ ሊንኮችን በመጫን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡
Facebook:- https://www.facebook.com/gurage1Zone
Website:- https://gurage.gov.et
Telegram:- https://t.me/comminuca
Youtub: -https://www.youtube.com/channel/UCzrcazGvvIO2tG7bQN36Cx

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *