ህዝበ ክርስቲያኑ የዘንድሮ የመስቀል በአል ሲያከብር ሀይማኖታዊ አስተምሮ በሚያዘዉ መሰረት ለከተማዉ ሰላም ፣ ልማት፣ አንድነትና ፍቅር እንዲመጣ ምዕመናን የበኩላቸዉን መወጣት እንዳለባቸዉ ተገለጸ።

መስከረም 16/2015 ዓ.ም

ህዝበ ክርስቲያኑ የዘንድሮ የመስቀል በአል ሲያከብር ሀይማኖታዊ አስተምሮ በሚያዘዉ መሰረት ለከተማዉ ሰላም ፣ ልማት፣ አንድነትና ፍቅር እንዲመጣ ምዕመናን የበኩላቸዉን መወጣት እንዳለባቸዉ ተገለጸ።

የደመራ በዓል በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ በልዩ ልዩ ሃይማኖታዊ ስርዓቶች ተከብሯል።

በደመራው ስርዓት ፕሮግራም ላይ የተገኙት የወልቂጤ ከተማ ከንቲባ አቶ አበበ አሰፋ እንዳሉት የመስቀል በአል በጉራጌ ማህበረሰብ ዘንድ ሀይማኖታዊና ባህላዊ ይዘት ያለዉ እንደሆነም አስረድተዋል።

የመስቀል በአል የሰላም ፣የፍቅር ፣የአንድነትና የእርቅ ምልክት ከመሆኑም በተጨማሪ የተጣላ ሰዉ የሚታረቅበት ነዉ መሆኑን ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የጉራጌ ሀገረ ስብከት ስራ አስኪያጅ መጋቢ ሳህሉ ተሠማ በበዓሉ እንደገለፁት መስቀልን የምናከብረው ጌታችን መድሃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ለኛ ሲል ቅዱስ ስጋው ተቆርሶበታል ፣ ቅዱስ ደሙ ፈስሶበታል ተሰቅሏል ለዚህም ታላቅ መንፈሳዊ ሚስጥሮች አሉት ብለዋል።

መስቀል የእግዚአብሔር ኃይል ነው መሰቀል የሠላም ተምሳሌት ፣ ክፉ መንፈስ የማረቅ ታላቅ መንፈሳዊ መሣሪያችን ነው ብለዋል።

በሀገራችን ኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች መስቀልን በቤተክርስቲያን ስነ ስርዓት መሠረት በአደባባይ በደስታ ማሳለፍ ያልቻሉ በጦርነት ቀጠና አካባቢ የሚኖሩ ክርስቲያን ወገኖቻችን ሠላም እንዲያገኙ በፀሎት ልናስባቸው ይገባል ብለዋል።

ቅድስት ቤተክርስቲያን ሁሉም የሀገራችንና ህዝቦቿን ሠላም እንዲሆኑ እንደ ወትሮዋ አጥብቃ ትፀልያለችም ሲሉ መልክታቸው አስተላልፈዋል።

በዓሉ ላይ የደመራ ችቦ የመለኮስና ጧፍ የማብራት ስነ-ስርዓት የተከናወነ ሲሆን ልዩ ልዩ ሃይማኖታዊ ትምህርቶችና ዝማሬዎችም ቀርበዋል።

አንዳንድ የበዓሉ ታዳሚዎች በሰጡት አሰተያየት የመስቀል በዓል ርህራሄን በመላበስ የተቸገሩ ጎረቤቶቻችንን በማገዝ በዓሉን በአብሮነት እያከበሩ መሆኑን ተናግረዋል ሲል የዘገበዉ የጉራጌ ዞን መንግስት ኮሚኒኬሽን መምሪያ ነዉ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *