ህዝበ ሙስሊሙ የአረፋ በዓል በሚያከብርበት ወቅት የማህበረሰቡን ማህበራዊና ባህላዊ እሴቶችን በማጎልበት እና አቅም የሌላቸውን ወገኖችን በመደገፍ ሊሆን እንደሚገባ የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ ገለጹ።

ሰኔ 21/2015

ህዝበ ሙስሊሙ የአረፋ በዓል በሚያከብርበት ወቅት የማህበረሰቡን ማህበራዊና ባህላዊ እሴቶችን በማጎልበት እና አቅም የሌላቸውን ወገኖችን በመደገፍ ሊሆን እንደሚገባ የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ ገለጹ።

የዘንድሮ የአረፋ በዓል የጉራጌ ዞን አስተዳደር ከወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በጉራጌ ዞን በእኖር ኤነር መገር ወረዳ በሚኢዲ ቀበሌ በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት ተከብሯል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በበዓሉ ተገኝተው እንዳሉት የአረፋ በዓል በዞኑ ባለፉት አመታት ባህላዊ ይዘቱን ሳይለቅ ለትውልድ ለማስተላለፍ በሚያስችል መልኩ ሲከበር ቆይቷል።

ህዝበ ሙስሊሙ በሀገሪቱ ሰላም፣ ልማትና እድገት ላይ እያበረከተ ያለውን ሚና ከፍተኛ ነው ያሉት ዋና አስተዳዳሪው በቀጣይ ከሌሎች እምነቶች ጋር ያለውን አንድነት ማጠናከር እንዳለበት ተናግረዋል።

ህዝበ ሙስሊሙ በዓሉ ሲያከብር ማህበራዊና ባህላዊ እሴቶቻችንን በማጎልበት በመከባበር፣ በመቻቻልና በመደጋገፍ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

እንደ አቶ ላጫ ጋሩማ ገለጻ የእምነቱ ተከታዮች በዓሉ ሲያከብሩ አቅም ለሌላቸው ወገኖች ማዕድ በማጋራትና በመርዳት ከማክበር ባለፈ የአከባቢያቸውን ሰላም ነቅተው መጠበቅ አለባቸው ብለዋል።

የወልቂጤ ዩንቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ፋሪስ ደሊል እንዳሉት የአረፋ በዓል ከሀይማኖታዊ በዓልነቱ ባሻገር በጉራጌ ማህበረሰብ ዘንድ ከፍ ያለ መስተጋብር ያለው በዓል እንደሆነ ገልጸዋል።

የአረፋ በዓል መገለጫው አንድ ሰው ለአረፋ በዓል ካስገባው የእርድ ስጋ ለድሃ የሚሰጥበት፣ ከጎረቤት፣ ከዘመድ አዝማድና ከሌላ እምነት ተከታዮቸ ጋር በመሆን በደስታ አብሮ በመብላትና በመጫወት የሚከበር በዓል ነው።

የደቡብ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አቡቶ አኒቶ የአረፋ በዓል በህዝበ ሙስሊሙ ዘንድ በድምቀት ከሚከበሩ በዓላት አንዱ ሲሆን በዓሉ ከሀይማኖታዊ እሴትነቱ ባለፈ ማህበራዊና ኢኪኖሚያዊ ጠቀሜታው ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

አረፋና ሌሎችም በዓላት የመቻቻል፣ የመከባበርና የአብሮነት እሴቶችን ከማጎልበታቸውም ባሻገር ለሀገር ግንባታ፣ ለሰላምና እድገት ያላቸው ሚና የላቀ እንደሆነ ጠቁመዋል።

የዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ መሰረት አመርጋ በበኩላቸው የጉራጌ ብሄረሰብ ጠንካራ ባህላዊ እሴት ያለው በመሆኑ የአረፋ በዓል ከዝግጅቱ ጀምሮ ከሌሎች ቤተ እምነቶች ጋር በመሆን ይከበራል።

ህዝበ ሙስሊሙ በመረዳዳት፣ በአብሮነትና ለተቸገሩ ወገኖችን በማካፈል የሚያከብሩት በዓል በመሆኑ ምስኪኖችና አቅመ ደካማ የህብረተሰብ ክፍሎች ጭምር በጉጉት የሚጠብቁት በዓል ነው።

የአረፋ በዓል ከፍ ብሎ እንዲከበርና እንዲተዋወቅ በዞኑ ላለፉት ተከታታይ አመታት ሲከበር መቆየቱን እስታውሰው በቀጣይ እንዲለማ፣ እንዲያድግ፣ እንዲሰነድና ባህላዊ ይዘቱን ሳይሸራረፍና ሳይበረዝ ለትውልድ እንዲተላለፍ እንደሚሰራ ኃላፊዋ ገልጸዋል።

የእኖር ኤነር መገር ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሸምሱ ሸሀቡ የኢትዮጵያ መገለጫ የሆነው መረዳዳትና መደጋገፍ ህዝበ ሙስሊሙ በበዓሉ ወቅት ተግባራዊ በማድረግ እንዲያከብር ጥሪ አስተላልፈዋል።

የጉራጌ ዞን እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ኡስታዝ ሀቢብ ሀጅህያር የአረፋ በዓል አሏህ(ሱወ) በደነገገው መሰረት ነብዩላህ ኢብራሂም(ሰወ) ልጃቸው እስማኤልን ለእርድ እንዲያቀርቡ ባዘዛቸው ሰዓት ነብዩላህ ኢብራሂም(ሰወ) ለአሏህ ተገዢ በመሆናቸው ትዕዛዙን በማክበር ልጃቸውን መስዋዕት ለማድረግ በማዘጋጀት ቢላዋ እንቢ ባለበት ወቅት ጅብሪል ከጀነት ምኩት አምጥቶ በልጃቸው ምትክ እንዲታረድ ትዕዛዝ የሰጠበት ዕለት ምክንያት በማድረግ ይከበራል ብለዋል።

ህዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከብር የተቸገሩትንና ምስኪኖችን ያለውን በማካፈልና በማሰብ ሊሆን እንደሚገባ ተናግረዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *