ህዝበ ሙስሊሙ የአረፋ በአል ካለምንም የጸጥታ ችግር በሰላም እንዲያከብር ህብረተሰቡ ከመቼዉም ጊዜ በላይ ከጸጥታ ሀይሉ ጋር ተቀናጅቶ የአካባቢዉን ሰላም መጠበቅ እንዳለበት የጉራጌ ዞን ሰላምና ጸጥታ መምሪያ አስታወቀ።

ሰኔ 16/2015 ዓ

በዞኑ በሁሉም አካባቢዎች የአረፋ በአል በሰላም እንዲጠናቀቅ በተደራጀ መልኩ የዞኑና የፌዴራል ጸጥታዉ አስከባሪ አካላት ተመድበዋል።

በአሉ በሰላም ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ የሚመለከታቸዉ የጸጥታ ባለድርሻ አካላት በወልቂጤ ከተማ ዉይይት አካሄደዋል።

የአረፋ በአል የአብሮነት፣የአንድነትና የመቻቻልን እሴት መሰረት ሲሆን በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ እጅግ በደመቀ ሁኔታ ከሌሎች እምነት ተከታዮች ጋር በአብሮነት ያከብሩታል።

የጉራጌ ዞን ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ሀላፊ አቶ አብድልሀፊዝ ሁሴን የዘንድሮ የአረፋ በአል ህዝበ ሙስሊሙ የአረፋ በአል ሲያከብር አቅመ ደካሞችን በማሰብ የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት ፣የመተሳሰብና የአብሮነት ባህላችን ከመቼዉም ጊዜ በተሻለ ሁኔታ አጠናክረዉ መቀጠል ይኖርባቸዋል ብለዋል።

የጉራጌ ብሔረሰብ የበርካታ እሴቶች ባለቤት ሲሆን ከነዚህም እሴቶች መካከል በየአመቱ በድምቀት የሚከበሩ የአረፋና የመስቀል በአላቶች ይጠቀሳሉ ብለዋል።

በአሉ ካለምንም የጸጥታ ችግር በሰላም እንዲጠናቀቅ ህብረተሰቡ ከመቼዉም ጊዜ በላይ ከጸጥታ ሀይሉ ጋር ተቀናጅቶ መስራት ይኖርበታል ብለዋል።

የበአል ወቅት እንደመሆኑ መጠን በዞኑ አሁን ላይ ያለዉ አንጻራዊ ሰላም ለማደፍረስና የህዝቡ ሰላም ለመበጥበጥ የሚንቀሳቀሱ ሀይሎች ካሉ ለጸጥታ መዋቀሩ ማህበረሰቡ አሳልፎ መስጠት ይኖርበታል።

የጉራጌ ዞን ፖሊስ መምሪያ ሀላፊ ኮማንደር ጠጄ በበኩላቸዉ የአረፋ በአል ለማክበር የተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል ከትመዉ በተለያዩ የስራ ዘርፍ ላይ ተሰማርተዉ የነበሩ የብሔረሰቡ ተወላጆች ወደ ትዉልድ ቄያቸዉ በመምጣት በአሉ በአብሮነት ያከብሩታል ብለዋል።

ለበአል ዝግጅት የሚያስፈልጉ ግብአት በምንሸምትበት ወቅት ባዕድ ነገሮች እየቀላቀሉ የሚሸጡ ህገ ወጦች የሚኖሩ ሲሆን ህብረተሰቡ ልዩ ጥንቃቄ አድርጎ መሸመት ይኖርበታል።

ህዝበ ሙስሊሙ ለበአል ዝግጅት በሚያደርጉበት ጊዜ በጥንቃቄ ጉድለት የእሳት አደጋ እንዳይፈጠር ልዩ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበትም አብራርተዋል።

በመጨረሻም በአሉን የሰላም የመቻቻል፣ ወላጅ አጥ ህጻናትንና አረጋዉያን በማሰብ ልናከብረዉ ይገባል ብለዋል

      የጥቆማ ስልክ 

0113300323: 0113300288:
0113300258 : 0113658137

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *