ህዝበ ሙስሊሙ በረመዳን ወቅት ያሳየው አብሮነት፣ አንድነትና መደጋገፍ በቀጣይም ይበልጥ በማጠናከር ለሀገር ሰላምና እድገት አትኩሮ እንዲሰራ ተገለጸ።

3ኛ ዙር ታላቅ የአብሮነትና የወንድማማችነት የጎዳና ላይ ኢፍጣር መርሃ ግብር በጉራጌ ዞን በወልቂጤ ከተማ ተካሂዷል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ሼህ አብድል ከሪም ሼህ በድረዲን በዚህ ወቅት እንደገለጹት ይህ ወር በሀገራችን የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮችና የእስልምና እምነት ተከታዮች ጾም በጋራ እየጾሙ መሆኑ ለየት ያደርገዋል ሲሉ ገልጸዋል።

ይህ ደሞ ለሀገራችን በረከት፣ ሰላም እና አብሮነት ከፍተኛ ሚና አለው ሲሉ ነው የተናገሩት።

የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመሰረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር መሀመድ ኑርዬ እንደገለፁት የረመዳን ወር መልካም ተግባራቶች የምናከናውንበት ወቅት በመሆኑ ይህንን ተግባር ከጾምም በኃላ አጠናክረን ልንተገብረው ይገባል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ከፍተኛ ፕሬዝዳንት ሀጅ መሀመድ ኸሊል እንዳሉት የጉራጌ ማህበረሰብ ሰለ አብሮነትና አንድነት አስተማሪ የሆነ ታላቅ ህዝብ በመሆኑ ህዝበ ሙስሊሙም ይህን ተግባር አጠናክሮ ማስቀጠል አለበት።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በፕሮግራሙ ተገኝተው ባስተላለፉት መልእክት እስልምና ትርጉሙ ሰላም ማለት ነው። በመሆኑም ሰለ ሰላም አብዝቶ የሚጨነቅ ህዝበ ሙስሊሙ ስለ ሰላም ባደረገው ንቁ ተሳትፎ በከተማው አንጻራዊ ሰላም ማምጣት ተችላሏ ብለዋል።

ይህንን በከተማው ብሎም በዞኑ የተገኘው አንጻራዊ ሰላም ህዝበ ሙስሊሙ አጠናክሮ እንዲያስቀጥል መልእክታቸውን አስተላልፏል።

የጉራጌ ዞን እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ሰብሳቢ ሼህ አባስ ናስር በንግግራቸው በዚህ የኢፍጣር ፕሮግራም ከ250 በላይ ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ኢፍጣር ተደርጓል።

በቀጣይም በአንድነት ፈጥረን፣ እጆቻችንና ፊታችን ወደ ፈጣሪ አዙረን ለሀገራችን ሰላም አበክረን ልንጸልይ ይገባል ያሉት ሼህ አባስ።

ይህን መረሀ ግብር በሰላም ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል ።

የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ እንዳለ ስጦታው የከተማው ልማትና እድገት ለመረጋገጥ ሁሉም ሰው እያደረገ ያለው አብሮነት፣ ወንድማማችነትና ሰላም ፈላጊነት አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የዛሬው የኢፋጣር መርሀ ግብር የከተማው ህዝብ አብሮነትንና አንድነት ያረጋገጠበት ታላቅ ፕሮግራም መሆኑን አመላክተዋል።

በኢፍጣር ወቅት አግኝተን ያነጋገርናቸው አካላት በበኩላቸው ይህ የኢፍጣር መርሀ ግብር አብሮነትና ወንድማማችነትን የሚገለጽበት እንዲሁም የተቸገሩትም በጋራ የሚያፈጥሩበት በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *