ህብረተሰቡ ጥራት ያለው የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲያገኝ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የስምሪት አሰጣጥ ስርአት (ኢ_ቲኬቲንግ) መጀመሩ የጉራጌ ዞን ትራንስፖርትና መንገድ ልማት መምሪያ አስታወቀ።

በትራንስፖርት ዘርፍ የተጀመረው የቴክኖሎጂ ስራ ውጤታማ እንዲሆንና ህገ ወጥነትን ለመከላከል ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል እገዛ ሊያደርግ እንደሚገባ መምሪያው አሳስቧል።

የጉራጌ ዞን ትራንስፖርትና መንገድ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙራድ ከድር እንደተናገሩት በዞኑ በትራንስፖርት ዘርፍ ለረጅም ጊዜ ሲስተዋል የነበረውን የመልካም አስተዳደር ችግርና ህገ ወጥ ስራዎች በህብረተሰቡ ዘንድ ቅሬታ ሲያስነሳ ቆይቷል።

ይህንን ችግር ጎልቶ ከሚታይባቸው አካባቢዎች አንዱ የወልቂጤ መናሀሪያ ሲሆን ከታሪፍ በላይ በማስከፈል ህብረተሰቡን ይበዘብዙ የነበሩ 88 ህገ ወጥ ደላሎች ከመናኸርያ የማስወጣት፣ በግቢው ውስጥ መቃሚያና ማጨሻ የነበሩ 32 ሸራዎችን የማፍረስና የተሽክርካሪዎች ስምሪት መርሀ ግብር በስብጥር እንዲወጣ መደረጉ አቶ ሙራድ ተናግረዋል።

በቴክኖሎጂ የተደገፈ የስምሪት አሰጣጥ ስርአት (ኢ_ቲኬቲንግ) መጀመሩ ህብረተሰቡ ከታሪፍ በላይ እንዳይከፍል፣ ተሳፋሪን ከእንግልት የሚታደግ ፣ትርፍ እንዳይጫን የሚያደርግ፣ ለወጣቶች የስራ እድል የሚፈጥር፣ ህገ ወጥ ደላሎች እንዳይኖሩ የሚያደርግና ዘመናዊ መናኸርያ እንዲፈጠር የጎላ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

መንግስት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የነዳጅ ድጎማ ያደረገ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው የመኪና ባለንብረቶች የሚያነሱዋቸው ጥያቄዎች ቢኖሩም አሁን በአለው ሁኔታ ግን እነሱን የማይጎዳ አለመሆኑና በሌሎች ጉዳዮችም ላይ ስምምነት ላይ መደረሱ አስታውቀዋል።

አቶ ሙራድ አክለውም በትራንስፖርት ዘርፍ የተጀመረው ህግ የማስከበርና የቴክኖሎጂ ስራ ውጤታማ እንዲሆንና ከስርአቱ ውጪ ትርፍ የሚያስከፍሉ ተሽከርካሪዎች ላይ ጥቆማ በመስጠት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል እገዛ ሊያደርግ እንደሚገባ መልእክታቸው አስተላልፏል።

የጉራጌ ዞን ትራንስፖርትና መንገድ ልማት መምሪያ ምክትልና የትራንስፖርት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አህመድ ሀሰን እንደገለፁት (የኢ- ቲኬቲንግ)ስራ ከመጀመሩ በፊት ስራው ቀጣይነት እንዲኖረውና ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ በርካታ ስራዎች ሲሰሩ ቆይቷል።

ይህ ቴክኖሎጂ(ኢ_ቲኬቲንግ) በደቡብ ክልል የመጀመርያው ሲሆን የትራንስፖርት ዘርፉ ከማዘመን በተጨማሪ ወጪ ፤ጉልበትና ጊዜ ቆጣቢ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ለአብነትም በህገ ወጥነት በተነሱ ቦታዎች ቲኬት የሚቆረጥባቸው ቤቶች ከማመቻቸት በተጨማሪ ከአሽከርካሪዎች ማህበር፣ የዞኑና የወልቂጤ ከተማ የትራፊክና የፖሊስ መዋቅሮች ውይይት ተደርጎ መግባባት ላይ ተደርሷል ያሉት አቶ አህመድ ሁሴን ከሀዲያ ዞን እና ከወሊሶ ከተማ የዘርፉ አመራሮች ጋር ተነጋግረናል ብለዋል።

የሰላም ሀገር ማህበር ስራ አስከያጅ አቶ ፍቃዱ ቴኒ እንዳሉት ከዚህ በፊት በወልቂጤ መናኸርያ የነበሩ ብልሹ አሰራሮች በመኖራቸው ሹፌር፣ እረዳት፣ባለሀብቶችና ህብረተሰቡ ተጠቃሚ እንዳይሆን አድርጓቸዋል።

ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ መሻሻሎች ቢኖሩም በዘላቂነት ችግሩ ለመቅረፍ ይህ ቴክኖሎጂ ግን መሰል አይነት ችግሮችን ለመቅረፍ እገዛ የሚያደርግ ሲሆን በቀጣይ ለተግባራዊነቱ የበኩላችን ድርሻ እንወጣለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ሲስተም አስተባባሪ አቶ ቢኒያም ፍቃዱ የወልቂጤ ቅርንጫፍ 13ኛው ሲሆን ቴክኖሎጂው ሚሰራው ለህብረተሰቡ በታሪፉ ልክ ቲኬት መቁረጥ፣ለመኪናዎች መውጫ መስጠትና ቅደም ተከተል የማሰያዝ ስራ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ቴክኖሎጂው ለህብረተሰቡ ቀልጣፋ አገልግሎት የሚሰጥ፣መናኸርያ ውስጥ ያሉ አካላቶች የስራ ጫና የሚቀንስ፣ሙሉ የመኪና መረጃዎችን የሚያሳውቅ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ሲሆን ተሳፋሪዎች ግንዛቤያቸው በማሳደግና ሲሳፈሩ ቲኬታቸው ቆርጠው መጓዝ እንዳለባቸው አስታውቋል።

ወጣት ካሊድ አበበ በወልቂጤ መናኸሪያ ኢ_ቲኬት ቆርጦ ሲሳፈር ያገኘነው ተጓዥ ሲሆን ቴክኖሎጂው በመተግበሩ ሹፌሮችና ተጓዦች ያለ ምንም ጭቅጭቅ በሰላም እንዲጓዙ ያደርጋል ብለዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *