ህብረተሰቡ የሚያነሳቸው መሰረታዊ የልማት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ዕቅድ አቅዶ በትኩረት እየሰራ መሆኑን የጉራጌ ዞን ፕላንና ልማት መምሪያ አስታወቀ።

የዞኑ የአስር አመት መሪ የልማት ዕቅድ ላይ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በወልቂጤ ከተማ ውይይት ተካሂዷል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ጀማል በውይይቱ ተገኝተው እንደተናገሩት በዞኑ የታቀደውን የአስር ዓመት የልማት ዕቅድ ለማሳካት ገቢ የመሰብሰብ አቅም በማሳደግ ማህበረሰቡ፣ መንግስታዊ ያልሆኑ የልማት ድርጅቶችና ባለድርሻ አካላት የነቃ ተሳትፎ ማድረግ አለባቸው ብለዋል።

አክለውም ህብረተሰቡን በምግብ ዕህል ራሱን እንዲችል የግብርና ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የሚያስችል የመካናይዜሽ ስራ ሊጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል።

አያይዘውም የዞኑ ህዝብ ባህል፣ ዕሴትና አንድነት የሚያጠናክሩ ስራዎች ላይ የተለየ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባም አቶ መሀመድ ጀማል አሳስበዋል።

የጉራጌ ዞን ፕላንና ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ከበደ ሀይሌ በበኩላቸው ህብረተሰቡ በተደጋጋሚ የሚያነሳቸው የልማት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት በተኩረት እየተሰራ ነው።

የዞኑ ማህበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛል ያሉት አቶ ከበደ እነዚህንም የዞኑ የአዳሪ ት/ቤት ግንባታ፣ የከሬብ፣ የመጌቻና የደመካሽ ሰፋፊ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች፣ በመንግስትና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች የተገነቡና በመገንባት ላይ የሚገኙ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች፣ የመንገድ ልማትና ሌሎችም ይገኙበታል ብለዋል።

እንደ አቶ ከበደ ሀይሌ ገለጻ በሚቀጥሉት አስር ዓመት የዞኑ ህዝብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ የልማት ስራዎች እንደሚሰራም ገልጸዋል።

እነዚህንም በአስር አመት መሪ የልማት ዕቅድ ለመተግበር ከታቀዱ ዋና ዋና ዕቅዶች መካከል የጤና ሳይንስ፣ የመምህራን ትምህርት ማሰልጠኛና የግብርና ሳይንስ ቴክኒክ ኮሌጆችን መክፈት፣ የደም ባንክ ማቋቋም እንዲሁም የማህበረሰብ ቴሌቪዥን ጣቢያ ለመገንባትና ሌሎችም ወሰራታዊ የሆኑ ስራዎች በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

አያይዘውም የዞኑ ገቢ የመሰብሰብ አቅም አሁን ካለበት 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ወደ 11 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ ማሳደግ፣ የግብርና ምርትና ምርታማነት በመሳደግ የማምረት አቅም ከ5 ነጥብ5 ሚሊዮን ኩታል ወደ 8 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩታል በላይ ምርት መሰብሰብ እንዲሁም የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ሽፋን አሁን ካለበት 36 ነጥብ 7 ከመቶ ወደ መቶ ፐርሰንት ለማድረስ መታቀዱን ተናግረዋል።

መንግስት የሚመድበው ውስን ሀብት የወጣቶች የስራ ዕድል በመፍጠር የህብረተሰቡ ልማት ሊያፋጥኑ በሚችሉ የልማት ዘርፎች ላይ ሊውል ይገባል ሲሉ አቶ ከበደ ተናግረዋል ።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት በዞኑ የታቀደውን የአስር ዓመት የልማት ዕቅድ ህብረተሰቡ በማሳተፍ እንዲሳካ ለማድረግ ከፍተኛ ርብርብ እንደሚያደርጉና በየደረጃው በዚህ እቅድ መነሻነት አካባቢያዊ እቅዶች በጥራት እንደሚያዘጋጁም ተናግረዋል።

በውይይቱም የዞን አመራሮች፣ የወረዳ አስተዳዳሪዎች፣ የከተማ አስተዳደር ከንቲባዎች፣ የፕላንና ልማት ጽ/ቤት ኃላፊዎች፣ የልማት ዕቅድ ባለሙያዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

= ኢትዮጵያን እናልማ!
= የፈረሰውን እንገንባ!
= ለፈተና እንዘጋጅ!
በተጨማሪም እነዚህ ሊንኮችን በመጫን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡
Facebook:- https://www.facebook.com/gurage1Zone
Website:- https://gurage.gov.et
Telegram:- https://t.me/comminuca
Youtub: -https://www.youtube.com/channel/UCzrcazGvvIO2tG7bQN36C

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *