ህብረተሰቡ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ በሚሰራጩ ሀሰተኛ መረጃዎች ሳይደናበር የአካባቢውን ሰላም ነቅቶ መጠበቅ እንዳለበት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ አሳሰበ፡፡


ህብረተሰቡ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ በሚሰራጩ ሀሰተኛ መረጃዎች ሳይደናበር የአካባቢውን ሰላም ነቅቶ መጠበቅ እንዳለበት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ አሳሰበ፡፡

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተመስገን ካሳ በክልሉ ወቅታዊ የፀጥታ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

አቶ ተመስገን በመግለጫቸው በወልቂጤ ከተማ፣ በአበሽጌና ሶዶ ወረዳዎች አካባቢ የሚስተዋሉ የፀጥታ ችግሮች በመከላከል ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የክልሉ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል፡፡

ከወልቂጤ ከተማ ወሰን ጋር ተያይዞ በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚሰራጩ መረጃዎች ፍፁም ሀሰት በመሆናቸው ህብረተሰቡ ከአሉባልታ መረጃዎች መራቅ ይጠበቅበታል።

መንግስት በከተማው ወሰን ላይ በግልፀኝነት ላይ የተመረኮዘ ውይይት እንደሚያደርግ ታውቆ በሀሰት ወሬ በከተማው የሰፈነው አንፃራዊ ሰላም እንዳይደፈርስ ህብረተሰቡ ነቅቶ መጠበቅ አለበት ብለዋል፡፡

በተለይም ከከተማው ወሰን ማስከበር ጋር ተያይዞ ቀን ቆርጠው በዚህ ቀን ሊካለል ነው፣ በዚህ ቀን ሽብር ይፈጠራል፣ ተጠንቀቁ፣ ተዘጋጁ እያሉ ህዝብን በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚያሸብሩ አካላት በመኖራቸው ህዝቡ በእነዚህ የአሉባልታ ወሬዎች ሳይደሸበር ከመንግስት የሚተላለፉ መረጃዎችና መልዕክቶችን ብቻ በመከታተል ሰላማዊ ኑሮውን መኖር አለበት ብለዋል፡፡

መንግስት ከህብረተሰቡ የተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የተለያዩ ጥናቶች እየተካሄዱ ሲሆን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየመከረም ይገኛል፡፡

ስለሆነም መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት እንዴት እና መቼ እንደሚወስን፣ ምነ አይነት ውሳኔ እንደሚወስን መንግስት ኃላፊነት ወስዶ በግልጽ ያሳውቃል ነው ሉት ኃላፊው፡፡

ይሁን እንጂ የከተማው ሰላም ለማደፍረስ በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ የሚወሰዱ እርምጃዎች እንደተጠበቁ መንግስት በሚወስነው ውሳኔ የሚፈጠር ሁከትና ብጥብጥ እንደማይኖር አረጋግጠዋል፡፡

በ2016 ዓ.ም በከተማው ተከስቶ የነበረው የፀጥታ ችግር ለመቅረፍ የክልሉ መንግስት ያደረገው ጥረት ከፍተኛ ስለነበረት በከተማው አንፃራዊ ሰላም ማስፈን የተቻለ በመሆኑ ህዝቡን ሊያሰጋ የሚችል የፀጥታ ችግር ሊፈጠር እንደማይችል ገልፀዋል፡፡

በጉራጌ ዞን አበሽጌ ወረዳ ተላላኪ ጽንፈኞች ከወረዳው አልፎ በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ዞንና ምዕራብ ሸዋ ዞን ኖኖና አመያ አካባቢዎች ላይ ጉዳት አድርሰዋል፡፡ ጉዳት አድራሾቹ በአበሽጌ ወረዳ የሚገኙ ጽንፈኛ ሀይሎች ብቻ ሳይሆን እዛው ከሚኖሩ ቡድኖች ጋር በመሆን ነው ብለዋል፡፡

ድርጊቱ የፈጸሙ አካላት ለህግ በማቅረብ የማጣራት ስራ እየተሰራ ሲሆን ህገወጥ ታጣቂዎችን ትጥቅ እያስፈታን ሲሆን ለእዚህ እኩይ ተግባር ተባባሪ የሆኑ በተለይም ስንቅ የሚያቀብሉ፣ በገንዘብ እና፣ በመሳሪያ የሚደግፉ አካላት መኖራቸው በመረጃ የተረጋገጠ በመሆኑ ተጠያቂ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

ይህንን የህግ አግባብ በማዛባት ጽንፈኞቹ በተወሰ ማህበረሰብ ላይ ብሄር ተኮር ጥቃት እንደተፈፀመ አድርገው ህዝቡ እንዳይረጋጋና የአካባቢው ሰላም ለማደፍረስ የሀሰት መረጃዎች በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች እያሰራጩ ይገኛሉ፡፡

እንደ አቶ ተመስገን ገለፃ አጥፊው ኃይል ከማህበረሰቡ እሴት ባፈነገጠ መልኩ የተለያዩ ወንጀሎች እየፈፀመ ነበር፡፡ ህግን ለማስከበር ከህብረተሰቡ ጋር የተለያዩ የውይይት መድረኮች የተዘጋጁ ሲሆን በህግ ማስከበር ላይ የጋራ መግባባት ተፈጥሮ ወደ ተግባር ተገብቷል፡፡

ህዝቡ ወንጀለኞችን አጋልጦ እየሰጠ በመሆኑ የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ከፌደራል የፀጥታ አካላት ጋር በመሆን የጀመረው ህግ የማስከበር ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

በተያያዘ በምስራቅ ጉራጌ ዞን ሶዶ ወረዳ ጽንፈኛ ሀይሎች ጨለማን ተገን አድርገው
የህይወት ጉዳት አድርሰዋል፡፡ ጉዳቱ የደረሰው በሶዶ ወረዳ የጀርሳ አካባቢ ሲሆን ከኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ጋር አዋሳኝ አካባቢ ነው፡፡

በአካባቢው ሰላም ለማስፈን ከኢሮሚያ ክልል ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የጋራ ጠላት በጋራ ለመከላከል እና በጋራ ለማደግ ያስችላል ብለዋል፡፡

ስለሆነም አጥፊ ኀይሎች ችግሩ ለማባባስ ችግሩ የተፈጠረው በማዕከላዊ ኢትዮጵያ እንደሆነና ብሄር ተኮር ጥቃት ተደርጎ የሚናፈሰው ወሬ መሰረተቢስ ነው ብለዋል፡፡

በመሆኑም ህብረተሰቡ በማህበራዊ ሚዲያዎች በሚሰራጩ የሀሰት ወሬዎች ሳይደናገር ጠላትን ለመመከት በቅንጅት መስራት ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡

የሀሰት መረጃ በሚያሰራጩ ቡድኖች ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *