ህብረተሰቡ በመሰረተልማት ስራዎች ተጠቃሚ ለማድረግ ባለሀብቶች በንቃት መሳተፍ እንዳለባቸው ተገለጸ ።

መጋ

በጉራጌ ዞን ጉመር ወረዳ 27 ሚሊዮን ብር በሆነ ወጪ በፊታውራሪ ኑር ሱልጣን የተገነባው የባድና የየሼ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታ ተጠናቆ አገልገሎት መስጠት ጀመረ።

የጉራጌ ዞን ዋና የመንግስት ተጠሪ አቶ መሰለጫካ እንደገለጹት የጉራጌ ማህበረሰብ የመንገድ፣ የውሃ፣ የትምህርትና የጤና ተቋማት በመገንባት የካበተ ልምድ ያለው ሲሆን በሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት እድገት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል ።

እንደ አቶ መሰለ ገለጻ የጉራጌ ባለሀብቶች የሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት እድገት ከማሳደግ ባለፈ የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግእየሰሩ ይገኛሉ። ከእነዚህ ባለሀብቶች መካከል ሃጅ ኑር ሱልጣን አንዱ ሲሆኑ በጉመር ወረዳ ሁለት ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች በማስቆፈር ህብረተሰቡ ተጠቃሚ በማድረግ ችለዋል።

የሁለቱ ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች ወጪ ሙሉ በሙሉ በመሸፈን የህብረተሰቡን የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር ተቀርፎ በማየታቸው መደሰታቸውን አቶ መሰለ ገልጸዋል።

የሰው ልጅ በቀዳሚነት ከሚያስፈልጉት መሰረታዊ ነገሮች አንዱ ውሃ ሲሆን የመንግሰት የልማት ክፍተት በመሙላት ረገድ እያደረገ ያለው አስተዋጽኦ አበረታች መሆኑን የዞኑ ዋና የመንግስት ተጠሪ ተነግረዋል።

በመሆኑም የጉራጌ ባለሀብቶች መዋዕለንዋያቸውን በዞኑ በማፍሰስ የህብረተሰቡ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ኃላፊነታቸው ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

ባለሀብቱ በዞኑ መዋዕለ ነዋዩን እንዱያፈስ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን ለዚህም በዞኑ ቀልጣፋና ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

የጉመር ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ፋይሰል ሀሰን በበኩላቸው ሃጅ ኑር ሱልጣን በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ከአንድ ሺህ 2 መቶ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች በገንዘብና በአይነት ከመደገፍ በተጨማሪ በተለያዩ የልማት ስራዎች በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ ብለዋል።

የልማት አርበኛ የሆኑት የሀጅ ኑር ሱልጣን መልካም ተሞክሮ ለሌሎች ባለሀብቶች ምሳሌ በመሆናቸው አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

በውሃ ፕሮጀክቱ ግንባታ የወረዳው አስተዳደር አስተዋጽኦ ባይኖረውም የህብረተሰቡ መሰረታዊ ችግር የነበረው የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር መቀረፉ እንዳስደሰታቸው አቶ ፈይሰል ተናግረዋል።

በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ የብሄሩ ተወላጅ ባለሀብቶች መንግስት ተደራሽ ባልሆነባቸው አካባቢዎች የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ለማድረግ የተከያዩ መሰረተልማት ስራዎች መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

ሃጅ ኑር ሱልጣን በአካባቢው የነበረውና የውሃ ችግር መቅረፍ የነበረው የልጅነት ህልም እውን ማድረግ በመቻላቸው ደስተኛ እንደሆኑ ተናግረዋል።

በቀጣይ በአካባቢው ሁለት ቀበሌዎች የሚያገናኝ ድልድይ ፣ የአከባቢው ማሕበረሰብ የመለገለገሉባቸው ሁለት ድንኬኖች፣ ወንበርና ሌሎች መሰረተ ልማቶች እንደሚያከናውኑ ተናግረዋል።

የወረዳው አስተዳደር የተገነባው የውሃ ፕሮጀክት ዘላቂ አገልግሎት መስጠት እንዲችል አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ማድረግ እንደሚጠበቅ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች በንጹሕ መጠጥ ውሃ እጥረት ምክንያት ለተለያዩ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጫና ተጋላጭ እንደነበሩ ገልጸው በባለሀብቱ የተገነባው የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት እረጅም የእግር ጉዞ እንዳስቀረላቸው ገልጸዋል።

በቀጣይም ሌሎች ባለሀብቶች መንግስት ባልደረሰባቸው አካባቢዎች ሰፋፊ የመሰረተ ልማቶች ስራዎች በማከናወን ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።

ሃጅ ኑር ሱልጣን ላበረከቱት አስተዋጽኦ የልማት ፊታውራሪ የማዕረግ ስም ተሰጥቷቸዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *