ህብረተሰቡን የሚያነሳቸውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ፈጣን ምላሽ እንዲያገኙ መንግስት በትኩረት መስራት እንዳለበት የጉራጌ ዞን የምክር ቤት አባላት አሳሰቡ።

መስከረም 8/2015
============≡
ህብረተሰቡን የሚያነሳቸውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ፈጣን ምላሽ እንዲያገኙ መንግስት በትኩረት መስራት እንዳለበት የጉራጌ ዞን የምክር ቤት አባላት አሳሰቡ።

የምክር ቤት አባላቱ የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ጀማል ያቀረቡት ሪፖርት መሰረት በማድረግ መንግስት የመብራት ተደራሽነት አለማስፋፋትና የመብራት መቆራረጥ ችግር መፍትሄ እንዲያገኝ መስራት እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል።

ሴቶች በኢኮኖሚው ዘርፍ እኩል ተጠቃሚና ተሳታፊ እንዲሆኑ በመስራትና የሚደርስባቸው የሃይል ጥቃትና የሚፈጸምባቸው ወንጀሎች መከላከል ይገባል ሲሉ አባላቶቹ አስገንዝበዋል።

ወጣቶች በስነምግባር እንዲታነጹ፣ በልማቱ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ማጠናከር ይገባል።

ከትምህርት አንጻርም ከቅርብ አመታት ጀምሮ የተማሪዎች ውጤት ማሽቆልቆልና መጠነ ማቋረጥ እየተበራከተ በመምጣቱ መንግስት ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት የተማሪዎች ውጤት ለማሻሻልና መጠነ ማቋረጥ ለመቀነስ መስራት ይጠበቅበታል ብለዋል አባላቱ።

የአርሶ አደሩ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተስተዋለ ያለው የማዳበርያ፣ የምርጥ ዘርና የተባይ መቆጣጠሪያ ኬሚካል በትኩረት ማቅረብ እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል።

ዞኑ አሁን ካለበት የጸጥታ ችግር እንዲወጣ አመራሩ፣ ህብረተሰቡና ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

በዞኑ የሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ የገቢ አሰባሰብ ተግባር፣ የፍራፍሬና ችግኝ ተከላ፣ የበጋ መስኖ ስንዴና ህዝቡ ከመከላከያ ሰራዊት ጎን ሆኖ እያደረገ ያለው ንቁ ተሳትፎ የሚበረታታ ነው ብለዋል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ጀማል ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት ከሰላምና ጸጥታ ስራዎች አንጻር በዞኑ በባለፉት አመታት ለመፍታት ጥረት መደረጉን ጠቁመው በቀጣይም በዞኑ በአንዳንድ አካባቢስዎች የሚስተዋሉ የሰላምና ጸጥታ ችግሮችን በመፍታት የህብረተሰቡን ሰላም ለማስጠበቅ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ከመብራት አቅርቦትና ተደራሽነት፣ ከትምህርት፣ ከመንገድ ተደራሽነትና ጥራት፣ ወደ አከባቢ የሚመጡ ኢንቨስትመንቶችን ፈጥኖ ወደ ስራ ከማስገባት አንጻር ያለውን ውስንነቶችን በቀጣይ የእቅድ አካል በማድረግ በትኩረት ይሰራልም ነው ያሉት።

ከሴቶች ተጠቃሚነትና ውሳኔ ሰጪነት አንጻር እንደ ዞኑ ውስንነት ያለበት በመሆኑ በቀጣይ የሴቶች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውና ውሳኔ ሰጪነታቸውን ላይ የበለጠ እንደሚሰራም አንስተዋል።

የአርሶ አደሩ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ከመካናይዜሽን፣ ከግብአት አቅርቦት፣ ከማዳበሪያ እዳ አንጻር ያሉ ክፍተቶች በቀጣይ እንደሚሰራም ተናግረዋል።

ለሴቶችና ወጣቶች የስራ እድል በሚፈጥር መልኩ ያልታረሱ የወል መሬቶችንና በኢንቨስትመንት ስም የተያዙ መሬቶችን ወደ ስራ እንዲገቡ የተጀመሩ ስራዎች የበለጠ በማስፋት እንደሚሰራም ገልጸዋል።

በበጀት አመቱ በወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች ያለውን የውሃ አቅርቦት ችግር ለመፍታት መንግስት፣ አጋር ድርጅቶች፣ ባለሀብቶችና ህብረተሰቡን በማስተባበር የተሰሩ ስራዎችና በቀጣይም በማስፋት የህብረተሰቡን የውሃ ችግር ለመቅረፍ ጥረት እንደሚደረግም አመላክተዋል።

የዞኑ ህዝብ አንድነትና እሴት የሚሸረሽሩ ተግባራትን በመቅረፍ የህብረተሰቡን አንድነትና እሴት የሚያጎለብት ስራ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

በመጨረሻም የዞኑ አስተዳደር ምክር ቤት የ2014ዓ.ም ሪፖርት በመገምገምና የ2015 የአስተዳደር ምክር ቤት እቅድ ለምክር ቤቱ አባላት በማቅረብ ጸድቋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *