ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ከመቼዉም ጊዜ በላይ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩበት እንደሚገባም የጉራጌ ዞን አስተዳደር አሳሰበ ።

የዞኑ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን የ2014 ዓመተ ምህረት የመጀመሪያ ግማሽ አመት እቅድ አፈጻጸም ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በቡታጅራ ከተማ መገምገሙን ተመልክቷል።

በመድረኩ የተገኙት የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሐመድ ጀማል እንደገለጹት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች የጤና አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግና የጤና መድህን ተጠቃሚ የአባላት ቁጥር ለማሳደግ አመራሮች ትኩረት ሰጥተው መስራት አለባቸው ።

የዞኑ ነዋሪዎች የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አባል በመሆን የሚጠበቅባቸውን መዋጮ በመክፈል የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ የአመራሩ በተለይም የወረዳና የከተማ አስተዳዳሪዎችና የዞን ደጋፊ አመራሮች ሚና የጎላ እንደሆነም አቶ መሀመድ አስገንዝበዋል።

ከዚህ ቀደም የአባላት መዋጮ የተሰበሰበባቸው ደረሰኞች ሙሉ በሙሉ አለመመለስ፣ አዳዲስ አባላት በሚፈለገው መጠን አለማፍራት፣ ከአባላቱ የተሰበሰበው ገንዘብ በወቅቱ ገቢ አለማድረግ፣ የጤና ተቋማት ለሚሰጧቸው አገልግሎቶች ክፍያ አለመፈጸምና አመራሩ የማዐጤመ ተግባር ትኩረት ሰጥቶ ያለመምራት ችግሮች እንደነበሩ ዋና አስተዳዳሪው አስረድተዋል።

ይሁን እንጂ በ2014 ዓመተ ምህረት የማዐጤመ የንቅናቄ መድረክ ከተካሄደ ወዲህ መሻሻሎች ቢኖሩም ህብረተሰቡ በተለይም በዝቅተኛ ደረጃ የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ፍትሃዊ የጤና አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ አለመቻሉን የተናገሩት አቶ መሐመድ በሚቀጥሉት ጊዜያት የዞኑ የማዐጤመ አፈጻጸም ወደ ሚፈለገው ደረጃ ለማድረስ በቁርጠኝነት መስራት ይገባል ብለዋል።

ዜጎች በህመማቸው ልክ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ማዐጤመ የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ በሁሉም የዞኑ መዋቅሮች አዳዲስ አባላት ከማፍራትና የነባሮቹ ውል ከማደስ ጎን ለጎን ከአባላቱ የሚሰበሰበው ገንዘብ ለታለመለት አላማ እንዲውል ማድረግ ይገባል ብለዋል ።

አያይዘውም አቶ መሀመድ የመስቃንና የማረቆ ወረዳ የህብረተሰብ ክፍሎች የማዐጤመ አገልገሎት ተጠቃሚ ለማድረግ የዞኑ አስተዳደር ይሰራል ብለዋል።

የዞኑ ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ሸምሱ አማን በበኩላቸው የማዐጤመ ተግባር ውጤታማ ለማድረግ በየጊዜው እየተገመገመ ግብረ መልስ ቢሰጥም የተሰጡ ግብረ መልሶች መነሻ በማድረግ የሚወሰዱ እርምጃዎች አጥጋቢ ባለመሆናቸው የዞኑን ማህበረሰብ የማይመጥንና ህብረተሰቡ በዘላቂነት የጤና አገልግሎት ተጠቃሚ አለማድረጉ ገልጸዋል።

አብዛኞቹ የዞኑ መዋቅሮች ማህበረሰባቸው ፍትሀዊ የሆነ የበጀት ድልድል የማውረድ ስራ ከሚሰራባቸው መንገዶች አንዱና ዋነኛው ተግባር የማዐጤመ አገልግሎት ነው ያሉት አቶ ሸምሱ በአግባቡ ከተተገበረ ሁሉም ማህበረሰብ በፍትሀዊነት ተጠቃሚ እንደሚያደርግ አብራርተዋል።

በዞኑ ውስጥ የነቃ ማህበረሰብ ፣ በየደረጃው የሰለጠነ የሰው ኃይልና በኢኮኖሚ ዘርፍ የላቀ ሚና የሚጫወት ማህበረሰብ ቢኖርም ዞኑን በማዐጤመ አፈጻጸም ዝቅተኛ ደረጃ ላይ መመደቡ ቁጭት ሊፈጥርብን ይገባል ብለዋል።

የኦዲት ግኝቶች አለመመለሳቸውና በግለሰቦች እጅ የሚገኝ ገንዘብ ገቢ ባለመደረጉ የጤና ተቋማት የገንዘብ እጥረት እንደገጠማቸው የገለፁት ኃላፊው አመራሩ እነዚህ ችግሮች በመቅረፍ ህብረተሰቡ መጥቀም አለብን ብለዋል።

አክለውም ኃላፊው ነጻ ታካሚዎች በፍትሀዊነት ተጠቃሚ ለማድረግ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙትን በአግባቡ መለየት ይገባል ብለዋል።

የቸሀ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙራድ ከድር፣ የማረቆ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ንጉሴ መኪ እና የቡታጅራ ከተማ ከንቲባ አቶ ነስሩ ጀማል በንቅናቄ መድረኩ ላይ ከተሳተፉት ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው።

እንደ ተሳታፊዎቹ ገለፃ የንቅናቄው መድረኩ የማዐጤመ ተግባር አመራሩ በበላይነት በመምራት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ወገኖች በፍትሀዊነት የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ እንሰራለን ብለዋል።

አመራሩ የማዐጤመ ተግባር ወጥነት ባለው አኳኋን ባለመምራቱ ውጤታማ መሆን እንዳልተቻለ የገለፁት ተሳታፊዎቹ የንቅናቄ መድረክ ከተካሄደ ወዲህ በደረሰኝ አመላለስ፣ በግለሰቦች እጅ የነበረው ገንዘብ እንዲመለስ ማድረግ፣ በአባላት ምዝገባና እድሳት ላይ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል ብለዋል።

በመሆኑም በቀጣይ ለዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠት የማዐጤመ አፈጻጸም ወደ ታቀደው ደረጃ ለማድረስ ተግተው እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።

= ኢትዮጵያን እናልማ!
= የፈረሰውን እንገንባ!
= ለፈተና እንዘጋጅ!

በተጨማሪም እነዚህ ሊንኮችን በመጫን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡
Facebook:- https://www.facebook.com/gurage1Zone
Website:- https://gurage.gov.et
Telegram:- https://t.me/comminuca
Youtub: -https://www.youtube.com/channel/UCzrcazGvvIO2tG7bQN36Cx

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *