ሀገርና ህዝብን በማስቀደም ለሰላም፣ ለልማትና ለህዝቦች አንድነት በጋራ እንደሚሰሩ በጉራጌ ዞን የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ገለጹ።

በዞኑ የሚንቀሳቀሱ የብልፅግና፣ የኢዜማ ፣የአብንና የእናት የፓለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት መደበኛ ሰብሰባቸውን በወልቂጤ ከተማ አካሂደዋል ።

በቀጣይ በሀገሪቱ ሊካሄድ የታሰበው ሀገራዊ የምክክር ውጤታማነት ሁሉም ፓርቲዎች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ እንሚገባ የጋራ ምክር ቤቱ አባላት ገለፁ።

የፓለቲካ ፓርቲዎቹ የጋራ ፎረም ሰብሳቢ አቶ ደምስስ ገበሬ የተኛውንም የልማትና የፖለቲካ ጥያቄ መመለስ የሚቻለው ሠላም ሲኖር መሆኑን በመገንዘብ ህዝብን ከህዝብ በማጋጨት በሀገርና በህዝብ አንድነት ላይ አደጋ ለመፍጠር በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ ሀሰተኛ መረጃዎችን ለመከላከል ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባ ገልፀዋል ።

ለዚህም በማህበራዊ ሚዲያ የፓርቲያችን ርዕዮተ አለምና አቋም ሊገልጹ የሚችሉ ትክክለኛና አውነተኛ መረጃዎችን ማጋራት ይገባል ብለዋል።

ሀይማኖትን ሽፋን በማድረግ በማህበረሰቡ መካከል ግጭት ለመፍጠር በሚሰሩ አካላት ላይ መንግስት ህግ የማስከበር ስራ መሰራት አለበት ብለዋል።

የጉራጌ ዞን የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢ አቶ መሰለ ጫካ በበኩላቸው ምንም እንኳን የፓለቲካ ፓርቲዎች የፓለቲካ ርዕዮታለም ቢለያይም አንድ በሚያደርጉ በሀገራዊና ዞናዊ የሠላምና የልማት ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ የመስራት ልምድ ማዳብር እንደሚገባ ገልፀዋል።

በተለይም በፓርቲዎች ጥላ ስር በመሆን የጥላቻ መረጃዎችን በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ አከላትን ለመቆጣጠርና ለማረም የፓለቲካ ፓርቲዎቹ የጋራ ምክር ቤቱ አባላት ኃላፊነት ወስደው ሊሰሩ ይገባልም ብለዋል።

በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ ህዝብን ከህዝብ ሊያጋጩ የሚችሉ ሀሰተኛ መረጃዎችን ለመከላከል ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባ በጉራጌ ዞን የሚንቀሳቀሱ የፓለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ፎረም አባላት ገለፁ።

የብልፅግና ፓርቲ ልማትና የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታን ነጣጥሎ አያይም ያሉት አቶ መሠለ እንደ ሀገር ህዝባችንን ተጠቃሚ ለማድረግ የተጣሉ ግቦችን ኦውን ለማድረግ የተጀመረው ጥረት በአንድ ፓርቲና በመንግስት ጥረት ብቻ እውን ሊሆን ስለማይችል ሁሉም ፓርቲዎች የድርሻቸው ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

የመድረኩ ተሳታፊ የነበሩ የተፎካካሪ የፓለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት በሰጡት አስተያየት የጥላቻ መልዕክት መነሻ ምክንያት አንዱ የልማት ጉድለት በመሆኑ መንግስት አቅሙን አሟጦ ከመጠቀምና ከመስራት ባሻገር ህዝባዊ ውይይት በማድረግ የተሻለ ተግባቦት መፈጠር አለበት ብለዋል።

የፓለቲካ ስልጣን የሚገኘው በህዝባዊ ምርጫ ብቻ መሆኑንና ህዝብንና ሀገርን ለአደጋ የሚያጋልጡ በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ መረጃዎችን አንደሚያወግዙ ተናግረዋል ።

በመድረኩ በዞኑ የሚስተዋሉ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል የዘገበው የጉራጌ ዞን መንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *