ሀገራችን ከስንዴ ልመና ለመታደግ በበጋ መስኖ ስንዴ የማልማቱ ስራ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ የጉራጌ ዞን አስተዳደር አስታወቀ፡፡

የበጋ መስኖ ስንዴ ዘር ማስጀመሪያ ፕሮግራም ከክልል፣ከዞንና ከወረዳ የተወጣጡ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት በዞኑ በጉመር ወረዳ በአበሱጃ ቀበሌ ተካሂዷል፡፡

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ጀማል በፕሮግራሙ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያ የተጋረጠባትን አደጋ ለመመከት እንደ ቀደምት አባቶቻችን ሁሉ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ደ/ር አብይ አህመድ ወደ ጦር ግንባር ሲዘምቱ መዝመት ያልቻለው አመራር የልማት ስራ እንዲያስተባብር ባስቀመጡት አቅጣጫ መሰረት በዞኑ በርካታ የልማት ስራዎች በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

በጦርነት ቀጠና ላይ የሚገኙ አርሶ አደሮች ከመደበኛ የእርሻ ስራቸው በመነጠል ምክንያት በሀገሪቱ የሚፈጠረውን የምግብ ዕህል ክፍተት ለመሸፈን እንዲቻል በዞኑ አንድም መሬት ጾሙን ሳያድር ሀገራችን ከስንዴ ልመና የሚታደጋትን የበጋ መስኖ ስንዴ የማልማቱ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ሲሉ ዋና አስተዳዳሪው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በዞኑ በሁሉም አካባቢ መሰረታዊ የውትድርና ስልጠና ወስደው የተመረቁ ህዝባዊ ሰራዊት ከጸጥታ አካላትና ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን ከልማት ስራ ጎን ለጎን የአካባቢያቸውን ሰላም ነቅተው እንዲጠብቁ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አቶ መሀመድ ጀማል ገልጸዋል፡፡

የበጋ መስኖ ስንዴ ዘር ማስጀመሪያ ፕሮግራም ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የደቡብ ክልል የግብርና ምርምር ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አግደው በቀለ እንደገለጹት የአርሶ አደሩ ምርታማነት የሚያድጉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በምግብ እህል እራሳችንን ችለን የስንዴ ልመና በቃ ሊባል ይገባል፡፡

በመሆኑም ይንን ለማሳካት የበጋ መስኖ ስንዴ የማልማቱ ስራ ከኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ጀምሮ በሁሉም ደረጃ በሚገኙ ከፍተኛ አመራሮች በተለየ ትኩረት የሚመሩት ተግባር መሆኑንም ዶክተር አግደው በቀለ አስገንዝበዋል፡፡

በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ በበኩላቸው የሀገሪቱ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት የሆነውን ግብርና ከዝናብ ጥገኝነት በማላቀቅ በመስኖ የማልማቱ ስራ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ስራ ከውጪ የሚገባውን ስንዴ ከመተካቱም ባለፈ ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል በመፍጠር የህዝቡ የኑሮ ደረጃ እንደሚያሻሽል አቶ አበራ ተናግረዋል፡፡

በዞኑ በ16 ወረዳዎች የተለያዩ የውሃ አማራጮችን በመጠቀም ከ2 ሺህ 1መቶ ሄክታር መሬት በላይ የበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት ተቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝ ምክትል አስተዳዳሪው ተናግረዋል፡፡

በጉመር ወረዳ አበሱጃ ቀበሌ የበጋ መስኖ ስንዴ ተደራጅተው ሲያለሙ ያገኘናቸው አርሶ አደሮች በሰጡት አስተያየት ከዚህ ቀደም በበጋ መስኖ ስንዴ አምርተው እንደማያውቁ ተናግረው ዘንድሮ የግብርና ባለሙያዎች በፈጠሩላቸው ግንዛቤ ወደ ስራ መግባታቸው ገልጸዋል፡፡

አክለውም አርሶ አደሮቹ እንደተናገሩት በበጋ መስኖ ስንዴ የማልማቱ ሰራ አጠናክሮ በማስቀጠል ከራሳቸው ፍጆታ ትርፍ በማምረት ለገበያ አቅርበው የሀገራቸውን የስንዴ ልመና ለማስቀረት እንደሚሰሩ ገልጸዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው፡፡
አካባቢህን ጠብቅ!

  • ወደ ግንባር ዝመት!
  • መከላከያን ደግፍ!

በተጨማሪም እነዚህ ሊንኮችን በመጫን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡
Facebook:- https://www.facebook.com/gurage1Zone
Website:- https://gurage.gov.et
Telegram:- https://t.me/comminuca
Youtub: -https://www.youtube.com/channel/UCzrcazGvvIO2tG7bQN36Cx

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *